የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎችና የተማሪ ቤተሰቦች የተደረገላቸውን አቀባበል አደነቁ

130

ነቀምቴ፣ ግንቦት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎችና የተማሪ ቤተሰቦች የተደረገላቸውን አቀባበል ከጠበቁት በላይ እንደሆነ በመግለጽ መደነቃቸውን አመለከቱ።

ተማሪዎቹና ቤተሰቦቻቸው በሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ከተማሪዎቹ መካከል ከደቡብ ሱዳን በነፃ የትምህርት ዕድል ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጣችው ተማሪ ቢአንካ ሴቢት በሰጠችው አስተያየት የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረጉላት አቀባበል የተረጋጋ መንፈስ እንደፈጠረላት ገልጻለች።

ከጅማ ከተማ የመጣችው ተማሪ ፈቲያ ቡልቱም በበኩሏ የተደረገላቸው አቀባበል ከጠበቀችው በላይ እንደሆነ ገልጻ፤ የቤተሰብነት ስሜት እንዳደረባት ጠቁማለች።

የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተማሪዎች ህብረት ተቀናጅተው ያደረጉላቸው መልካም አቀባበል ህብረተሰቡ ከተማሪዎች ጋር የጠበቀ ትስስር እንዳለው ለመረዳት እንዳስቻላት የገለጸችው ደግሞ ከባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ የመጣችሁ ተማሪ አጅመሊያ አወል ናት።

ከምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ ታናሽ እህታቸውን ይዘው የመጡት ወይዘሮ ለምለም ጅራታ የተደረገላቸው አቀባበል ቤተሰብ ስጋት እንዳያድርበት የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ እንደ አባትና እናት ሆኖ እንደሚይዛቸው እምነት ማሳደራቸውንም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ታናሽ ወንድማቸውን ለመሸኘት ከምዕራብ ወለጋ ዞን የመጡት አቶ መገርሳ ኦልጅራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ አስተማማኝ ዋስትና ለመሆን ያደረገውን ዝግጅት አድንቀዋል።

ለተማሪዎችና ለቤተሰቦች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መልካ ሂካ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን ሰላማዊ ለማድረግና የተማሪውን ደህንነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ተማሪዎችና የተማሪ  ወላጆች ምንም የሚያሳስባቸው ነገር እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዩኒቨርሲቲው የራሱን ተሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ፣ ሻምቡ፣ መንዲና ደምቢ ዶሎ በመላክ እየተቀበለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም