በአስተዳደሩ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ

97

ሰቆጣ፤ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 295 ሺህ ሰዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ እንዳሉት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ዛሬ በዘመቻ የተጀመረው “ኢቪኮሆል” የተሰኘው ክትባት ለተከታታይ 7 ቀናት የሚሰጥ ነው።

ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆናቸው ከ295 ሺህ በላይ ሰዎችን ለመከተብ ታቅዶ ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ክትባቱም እየተሰጠ ያለው በሰቆጣ ዙሪያ፣ ጋዝጊብላ፣ ዳህና፣ ሳህላ ሰየምት እና ዝቋላ ወረዳዎች እንዲሁም በሰቆጣና አምደወርቅ ከተማ አስተዳደሮች መሆኑንም አስታውቀዋል።

ክትባቱን የሚሰጡ ከ800 በላይ የጤና ባለሙያዎችና ደጋፊ ባለሙያዎችም መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።

የክትባት ዘመቻውን ያስጀመሩት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን ናቸው።

ክትባቱን ህፃናት፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ሊወስዱ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ሹመት፣ ህብረተሰቡ ክትባቱን በመውሰድ ጤናውን እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል።

በሰቆጣ ከተማ የሚኖሩት አቶ ሙላት ሃይሉ በአሁኑ ወቅት በከተማው የሰው መጨናነቅ እየታየ መሆኑን ጠቁመው፤ ክትባቱ ሊከሰት ከሚችል ተላላፊ በሽታ እንደሚከላከላቸው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ክትባቱ በአፍ ጠብታ የሚሰጥ መሆኑ ህጻናትም ሆነ አዋቂዎች በብዛት እንዲከተቡ የሚያነሳሳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ወጣት አየልኝ አባተ በበኩሉ መጭው የክረምት ወቅት በመሆኑ በንፅህና ጉድለት ምክንያት ሊከሰት ከሚችል ተላላፊ በሽታ ራሱን ለመጠበቅ መከተቡን ተናግሯል።

እንደ ወጣቱ ገለጻ ክትባቱ ቀድሞ መሰጠቱ ዜጎችን ከበሽታ ቀድሞ የመከላከል ሚናው የጎላ ነው።

በአሸባሪው ህወሓት የሽብር ቡድን ተፈናቀለው የመጡ ወገኖች ጭምር የክትባቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸው ተገልጿል።