የኢትዮጵያን ክብርና ነጻነት ጠብቀው ላቆዩ አባቶች ተገቢውን ክብር ልንሰጣቸው ይገባል

214

ግንቦት 15/2014/ኢዜአ/  የኢትዮጵያን ክብርና ነጻነት ጠብቀው ላቆዩ አባቶች ተገቢውን ክብር ልንሰጣቸው ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረው የአባቶች ቀን አባቶችን ጋቢ በማልበስ፣ በመንከባከብና ታሪካቸውን በማውሳት ለተከታታይ ቀናት ይከበራል።

የአባቶች ቀን “ክብር ለአባትነት” በሚል መሪ ሃሳብ በእንረዳዳ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተከብሯል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፤ በመርሃ-ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያን ክብርና ነጻነት ጠብቀው ላቆዩ አባቶች እገዛና ተገቢውን ክብር ልንሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

የአባቶች ቀን በኢትዮጵያ ላለፉት 13 ዓመታት መከበሩን አስታውሰው፤ እለቱን ስናከብር አገር ለማቆየትና ትውልድ ለማስቀጠል ለከፈሉት ዋጋ ተገቢውን ክብር በመስጠት መሆን አለበት ነው ያሉት።

የህይወት ተሞክሯቸው፣ እውቀትና ልምዳቸው እንዲሁም ለአገራቸው አንድነት የነበራቸው ቁርጠኝነት ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ እሴት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

በአስቸጋሪ ህይወት ኑሯቸውን እየመሩ የሚገኙ አረጋውያንን መንግስት በዘላቂነት ለመደገፍ ፖሊሲ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የማኅበረሰቡ ድጋፍና እገዛም ወሳኝነት አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አባቶች ቀን መሥራች አቶ እዮብ አርጋው፤ እለቱ አባቶችን በመንከባከብ በቀጣይ ተከታታይ ቀናት እንደሚከበር ገልጸዋል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም በሚካሄደው መርሃ-ግብር አባቶችን ጋቢ በማልበስ፣ በመንከባከብና ታሪካቸውን በማውሳት ይከበራል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት አባቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እየታወሰ ልዩ ክብር በመሰጠቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ታሪክ ከቆዩት አባትና እናቶች ጠይቆ በመረዳት ወጣቶች የአገራቸውን ስምና ክብር ተቀብለው እንዲያስቀጥሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአባቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በተለያዩ የዓለም አገራት በተለያዩ ቀናት የሚከበር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአዲስ አበባ እለቱ የተከበረበት "እንረዳዳ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር" በ1990 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን አሁን ላይ 814 አረጋውያን እና 1 ሺህ 600 ህጻናትን በመንከባከብ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም