ዲጂታል ኢኮኖሚን መሠረት ያደረገ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

91

ግንቦት 15/2014/ኢዜአ/  የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዲጂታል ኢኮኖሚን መሠረት ያደረገ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሥምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፋሪያት ካሚልና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ፈርመውታል።

ሥምምነቱ ዲጂታል ኢኮኖሚውን መሠረት ያደረገ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጎለብት የሚያግዝ ነው ተብሏል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፋሪያት እንደገለጹት የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛት በማብቃት የአገሪቱን እድገት ለማፋጠን በትኩረት እየተሰራ ነው።

ዘመኑ የሚፈልገውን የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚያሰርጹና እሴት የሚጨምሩ ሙያተኞችን ለማፍራትም ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።  

ዲጂታል ኢኮኖሚው የሚፈልጋቸው የሥራ ዘርፎችንና አይነቶችን በመለየት የሥራ እድልን ለመፍጠር ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዛሬ የተደረገው ሥምምነትም የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ የታቀዱ እቅዶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በማስረጽ ዘመኑ የሚፈልገውን የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

በሥምምነቱ መሰረት በጋራ የሚሰሩ ሥራዎች ተለይተው ትግበራን በሚመለከት ከወዲሁ ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጡ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን አስረድተዋል።

ይህንንም ተግባር ለማቀላጠፍ የሚያስችል የሥራ መመሪያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ያሉት ሚኒስትሩ   ለሥምምነቱ ስኬታማነት ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም