በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ5 ሺህ በላይ ሊትር ቤንዚን ተያዘ

112

ሆሳዕና፣  ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ) በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ5 ሺህ 500 ሊትር በላይ ቤንዚን ከነአሽከርካሪው መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

በሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ሹክረላ ሱጋቶ ቤንዚኑ ሊያዝ የቻለው በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ባደረገው ክትትል ነው።

መነሻውን ሻሸመኔ በማድረግ 5 ሺህ 520 ሊትር ቤንዚን በህገወጥ መንገድ ጭኖ ሲያጓጉዝ የነበረው አሽከርካሪም ትናንት ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ ከነመኪናው ተይዟል።

ህገ ወጥ ቤንዚኑን ጭኖ ከሻሸመኔ በመነሳት ከተማውን አቋርጦ ወደ ወላይታ መስመር ይጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-55485 አ.አ የሆነ አይሱዙ የጭነት መኪና መሆኑንም ገልጸዋል።

ዋና ሳጂን ሹክረላ እንዳሉት የመኪናው አሽከርካሪ ከነ ነዳጁ በቁጥጥር ስር የዋለው በከተማው ዋንዛ በር ቀበሌ በተለምዶ የአብስራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በአሽከርካሪው ላይ የምርመራ ስራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ቤንዚንን ጨምሮ ሌሎች በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር እጥረት እንዲከሰት የሚሰሩ ስግብግቦችን በማጋለጥ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ የሚስተዋለውን ክፍተትም የሚመለከተው አካል ተገቢ ቁጥጥር በማድረግ በህገ ወጦች ላይ እርምጃ በመውሰድ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።