በአሥር ወራት ውስጥ ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን በላይ ገቢና ወጪ እቃዎች ተጓጉዘዋል

102

ግንቦት 15/2014/ኢዜአ/ ባለፉት አሥር ወራት ውስጥ ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን በላይ ገቢና ወጪ እቃዎችን ማጓጓዙን የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ገለጸ።

በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የኦፐሬሽን ኃላፊ ተሾመ እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በዋናነት ጭነትና መንገደኞች ማጓጓዝ ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል።

ባለፉት አሥር ወራት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን በላይ እቃ ማጓጓዙን ገልጸው፤ ጎን ለጎንም ከ140 ሺህ በላይ መንገደኞችንም ማስተናገዱን አስረድተዋል።

ድርጅቱ ከሚሰጣቸው ሁለቱ አገልግሎቶችም 1 ነጥብ 53 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ገቢ ውስጥ 95 በመቶ ከጭነት ሲሆን ቀሪው 5 በመቶ ደግሞ ከመንገደኞች አገልግሎት የተገኘ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በብትን ወደ ውጭ የሚላኩ እቃዎችን በኮንቴነሮች አሽጎ በመላክ ለዚሁ የሚወጣውን ገንዘብ ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል።

ለአብነት ቡናን 98 በመቶ የሚሆነውን አሽጎ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው በማድረስ 111 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በአሥሩ ወራት ውስጥ 10 ሺህ 700 የሚሆኑ ባለ ሃያ ጫማ ኮንቴነሮች ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ መጓጓዛቸውን  ተናግረዋል።

እነዚህ እቃዎች በመኪና ቢጓጓዙ ኢትዮጵያ ወደ 660 ሚልየን ብር የሚሆን ወጪ ታወጣ ነበር ያሉት ኃላፊው በባቡር እቃዎቹን በማጓጓዝ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በጸጥታ ችግር፣ በመሰረተ-ልማት ስርቆትና መስመሩን ተገቢ ባልሆነ ቦታ ቆርጦ በመግባት በሚደርሱ አደጋዎች እየተፈተነ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በሥፍራው የጸጥታ አካላትን የሚያግዙ ከ500 በላይ አጋዥ ኃይሎችን በየአካባቢው በመቅጠር ሥርቆትን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ንብረቱን እንደራሱ እንዲያይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አዲስ አበባንና ጅቡቲ ከተማን የሚያያይዝ ሲሆን ለሸቀጦች ማጓጓዣ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ጭነት በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ የሚያስችል የትራንስፖርት ዘርፍ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም