የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች በአርሲ ዞን ስሬ ወረዳ ዘመናዊ ቤተመፃሕፍት ለማስገንባት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ አሰባሰቡ

113


ግንቦት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖን ጨምሮ ምሁራን እና ባለሐብት የአርሲ ዞን ስሬ ወረዳ ተወላጆች ለሚያስገነቡት ዘመናዊ ቤተመፃሕፍት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ አሰባሰቡ።


የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ምሁራን፤ባለሃብቶችና ሠራተኞች 50ኛ ዓመት የስሬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምስረታን ምክንያት በማድረግ ነው ለቤተ መፃሕፍት ግንባታው ገቢውን ያሰባሰቡት።


በገቢ ማሳባሰቢያ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን ጨምሮ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ምሁራኖችና ባለሃብቶች ተገኝተዋል።


የአርሲ ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሁሴን አህመድ እንደገለፁት በዞኑ በአካባቢው ተወላጆችና ህብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ የትምህርት ተቋማት እየተገነቡ ነው።


በዚህም የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ጥራቱን ለማስጠበቅ የአርሲ ዞን ተወላጆች ቤተ መፃሕፍት፤ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግሯል ።


የዞኑ ተወላጆች የመማር ማስተማር ሂደቱን በመደገፍና በማገዝ ረገድ እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል ።


በአርሲ ዞን የስሬ ወረዳ ተወላጅና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው የገቢ ማሰባሰብ ስራው የተከናወነው የስሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ቤተ መፃሕፍት እንዲኖረውና ትውልድን በተገቢው ዕውቀት ለማነፅ የሚጠበቅብንን ለማገዝ ነው ብለዋል።


በተለይ ሳይማር ያስተማረንን የወረዳውን ህብረተሰብ ለመካስና በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ያለው ተተኪው ትውልድ ራእይ እንዲኖረውና በርትቶ እንዲማር ሞራል ለመሆን ጭምር ነው ብለዋል።


ለዚህም የወረዳው ተወላጆች፤ባለሃብቶችና ምሁራን 50ኛ ዓመት የስሬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምስረታ ቀንን ምክንያት በማድረግ ትምህርት ቤቱ ዘመናዊ ቤተ መፃሕፍት እንዲኖረው ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ገቢ አሰባስበናል ብለዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም