የአዳማ ከተማን በማዘመን የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ አለብን- አቶ አዲሱ አረጋ

179

ግንቦት 15 ቀን 2014(ኢዜአ) የአዳማ ከተማን በማዘመን የህዝብ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ አለብን ሲሉ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለፁ።

በአቶ አዲሱ አረጋ የተመራ የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ልዑክ የአዳማ ከተማን የዲጂታላይዜሽን ስራ ጉብኝት ያካሄደ ሲሆን በዚህ ወቅት አቶ አዲሱ “በክልሉ ከተሞች ዘርፈ ብዙ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ብልሹ አሰራርና ሌብነትን ለማስወገድ የአገልግሎት አሰጣጣችንን ወደ ዲጂታላይዜሽ መቀየር አለብን” ብለዋል ።

''ህዝቡ ከመንግስት የሚጠብቀው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ነው ያሉት አቶ አዲሱ ይሄንን እውን ለማድረግ የምንችለው አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ስንችል ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ በተለይ በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣በመዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ገቢዎችና የንግድ ተቋማትን ወደ ዲጂታላይዜሽን በማስገባት ረገድ ያሉ ጅምር ጥረቶች የሚበረታቱና ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል ።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የከተማዋን አገልግሎት ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመቀየር ያስፈለገው የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ነው ብለዋል።

በዚህም የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ካዳስተር ስርዓት፣የገቢና የንግድ ተቋማት ማዘመንና ከህዝብ አገልግሎት ጋር የተቆራኙ ተቋማትን ወደ ዲጂታል የማስገባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወንጀልና ህገ ወጥ አሰራርን ለመከላከል የአዳማ ከተማን መሰረት ያደረገ አዳማ ፖርታል የመረጃ መቀበያ ሲስተም መዘርጋቱንም ከንቲባው ገልጸው፤ ዲጂታል መታወቂያ ካርድ በቴክኖሎጂ ተደግፎ እየተሰጠ መሆኑንና ዘመናዊ የቤቶች አስተዳደር ስርዓት፣የገቢ አሰባሰብና ማሻሻያ ላይ አዲስ ሶፍትዌር በማበልፀግ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም