ፈተናዎችን ተጋፍጦ የሚያሻግር ጠንካራና የበሰለ አመራር ለመፍጠር እየተሰራ ነው

112

ግንቦት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተለያዩ ፈተናዎችን ተጋፍጦ የሚያሻግር የበሰለና ጠንካራ አመራር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ገለጸ።

በክልሉ “አዲስ ፖለቲካዊ እይታ ለአዲስ ሀገራዊ እምርታ” በሚል መሪ ቃል የሚሰጥ የብልጽግና አመራሮች ስልጠና ተጀምሯል።

ስልጠናው በተርጫ፣ ቦንጋና ሚዛን ከተሞች በሦስት ማዕከል የሚሰጥ ሲሆን ከ800 በላይ አመራሮች ይሳተፉበታል ተብሏል።

በሚዛን አማን የስልጠና ማዕከል የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተደድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያን ከፈተናዎቿ ሊያሻግር የሚችል ብቁ አመራር መፍጠር የብልጽግና ፓርቲ አንዱ አቅጣጫ ነው።

May be an image of 2 people and people sitting

በመጀመሪያ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የተቀመጡ የሥራ አቅጣጫዎችን በዕቅድ በመያዝ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸው “በአግባቡ መተግበር እንዲቻል የአመራር የመሪነት ሚናን ከፍ የሚያደርግ ስልጠና እየተሰጠ ነው” ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው ስልጠና ሶስተኛ ዙር የአመራር ስልጠና መሆኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ በፓርቲው እሳቤና አሠራር ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ ኖሮት የህዝብ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የመጀመሪያ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤን ተከትሎ የወጡ እቅዶች የአመራር ትጋትና ተቀራራቢ የሆነ ከፍተኛ የመፈጸም አቅም የሚጠይቁ እንደሆነ አመላክተዋል።

አመራር ወጥ የሆነ አለም አቀፍ፣አህጉራዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመረዳት የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ እና የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተዘራ ወልደማርያም ናቸው።

May be an image of 1 person and indoor

“ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚሰጠው የስልጠና መድረክ አመራሮች የመፈጸምና ማስፈጸም አቅማቸውን አጎልብተው በህብረተሰቡ ዘንድ በተግባር እንዲያሳዩ ይደረጋል” ብለዋል።

የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማ ያደረገው የአመራር ስልጠናው የፓርቲውን ርዕዮት ተገንዝቦ ለውጡን መምራትና ማስቀጠል እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ለመጠገን ተግዳሮቶችን ተጋፍጦ ወደ መልካም ዕድል ቀይሮ ማሸነፍ እንደሚገባ ነው አቶ ተዘራ ያስታወቁት።

ለዚህም በ”በቅቶ የማብቃት” የፓርቲው ስትራቴጂን ተደግፎ በአዲስ እይታ ለአዲስ ሀገራዊ እምርታ አመራሩ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ሚዛን አማን ማዕከል በሚሰጠው ስልጠና ከቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ሸካ ዞኖች የተወጣጡ ከ220 በላይ የፓርቲው አመራሮች ይሳተፋሉ።