የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በሲዳማ ክልል የኢንተርፕራይዞችን የልማት እንቅስቃሴ እየጎበኙ ነው

101

ሀዋሳ ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የባለሀብቶችንና የኢንተርፕራይዞችን የልማት እንቅስቃሴ እየጎበኙ ነው።

የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ስልጠና እየወሰዱ ሲሆን ከስልጠናው ጎንለጎን አመራሮቹ በክልሉ የባለሀብቶችንና የኢንተርፕራይዞችን የልማት እንቅስቃሴ  በመጎብኘት ላይ ናቸው።

ታቦር የሴራሚክስ ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴና የማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲሁም አዳሬ እንስሳት እርባታና መኖ ልማት ህብረት ስራ ዩኒየን ደግሞ እየተጎበኙ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል ናቸው።

በጉብኝቱ ወቅት የሲዳማ ክልል እንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተክሌ ጆንባ እንዳሉት ዩኒየኑ በ2012ዓ.ም በ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ካፒታል የተቋቋመ ነዉ።

ዩኑየኑ በስራ እንቅስቃሴው ውጤታማ በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካፒታሉን 20 ሚሊዮን ብር በማድረስ እንደ ሀገር ሞዴል ለመሆን የበቃ ነው ብለዋል።

212 አባላት ያሉት አዳሬ እንስሳት እርባታና መኖ ልማት ህብረት ስራ ዩኒየን በአሁኑ ወቅት 450 የሚታለቡ ላሞች ያሉትና በቀን እሰከ 3ሺህ 500 ሊትር ወተት ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል።

May be an image of 3 people, tree and outdoors

በጉብኝቱ የሀዋሳ እንዲስትሪ ፓርክ፣ ይርጋለም የተቀናጀ ኢንዲስትሪ ፓርክ እንዲሁም ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ ይደረጋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ የሚመራው አመራሩ ከክልሉ ከ37 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጣ ነው።

የጉብኝቱ አላማም በየደረጃዉ የሚገኘው አመራር ከሞዴል ኢንተርፕራይዞች ያለውን ምርጥ ተሞክሮ በመቅሰምና በመቀመር በአካባቢው እንዲያስፋፋ የተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም