አፋርን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

115

ሰመራ፣ ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ)---አፋርን በቀጣይ አሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ተቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።


10ኛው ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ኮንፈረንስ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር አፋር የሁሉም አይነት የቱሪዝም መስህቦች ባለቤት ቢሆንም ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ገልጸዋል።

አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የቱሪዝም ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሥራዎች ባለመሰራታቸው የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።


"ክልሉ በዘርፉ ከበይ-ተመልካችነት ወጥቶና ያሉትን የቱሪስት ፀጋዎች አልምቶ የህብረተሰቡን ኑሮ መደገፍ አለበት" ብለዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ ክልላዊና ሀገራዊ እድገቱን መደገፍ እንዲችል የተለያዩ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ክልሉን የሀገሪቱ ተቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባራዊ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።


ሀላፊው እንዳሉት በአስር ዓመቱ መጨረሻ ክልሉን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር በ2011 ዓ.ም ከነበረው 12ሺህ ወደ 80ሺህ ለማሳደግ ታቅዷል።


ለዚህም በክልሉ ያሉ የቱሪስት ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሥራዎች ከወዲሁ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

"የተመረጡ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት የሚረዱ የተለያዩ ሥራዎችም ከፌደራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማከናወን ወደተግባር ተገብቷል" ብለዋል።


ለእዚህም የሉሲ መካነ-ቅርስ በተገኘበት "ሃዳር" ላይ የሉሲ ሙዚየም ለመገንባት የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ግንባታውን ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።


በተጨማሪም ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር "ከፈንታሌ እስከ ኤርታሌ" የሚል ፕሮጀክት ተቀርጾ አካባቢዎቹን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

ዳያስፓራውን በዘርፉ ልማት ለማሳተፍ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በቅርቡም በአካባቢዎቹ የሄሊኮፍተር ማረፊያ የሚሆን ጥርጊያ ሜዳም መዘጋጀቱን አስረድተዋል።


በተጨማሪም በአፋምቦ ወረዳ አዞና ሌሎች ብዘሃ-ህይወት የሚገኝባቸውን የገመሬ፣ ቦሃ እና አቢ ሐይቆችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል መታቀዱን አቶ አህመድ ገልጸዋል።

አካባቢውን ለቱሪስቶች የበለጠ ምቹና ሳቢ እንዲሆን የህብረተሰቡን ባህልና ወግ የሚያንጸባርቁ መዝናኛዎችን ለመገንባት ባለሃብቶችን የመሳብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።


ከሰመራ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው የአለሎበድ ፍልውሃ ለጤና ቱሪዝም እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ወደ ፍልውሃው የሚወስድ የጥርጊያ መንገድ በዚህ ዓመት መሰራቱንም ገልጸዋል።

ባለሃብቶችም በአካባቢው በአገልግሎት ዘርፉ እንዲሰማሩ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የቢሮው ሃላፊው ተናግረዋል።


ክልሉ በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች መሬት በነጻ ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የቱሪዝም ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በአፋምቦ ወረዳ የሚገኘውን የገመሬና ቦሃ ሐይቅ ጎብኝተዋል።

የወረዳው አስተዳደር አቶ ሁሴን አሊ ወረዳው ባለው እምቅ የቱሪዝም ሃብት የወረዳው ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በባህላዊ የዕደጥበብ ውጤት፣ በአስጎብኚነትና ተያያዥ የስራ መስኮች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

 
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሀመድ ኡስማን በበኩላቸው ክልሉን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን ዩኒቨርሲቲው በተለያየ መንገድ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

"በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች ለሚገኙ ወጣቶች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ስልጠናዎችን በመስጠት ተቋሙ ድጋፍ ያደርጋል።" ብለዋል።


ከእዚህ በተጨማሪ ህብረተሱቡ ባህላዊ ምግቦችን በዘመናዊ መልኩ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን በሚችልበትን አግባብ ዩኒቨርሰቲው እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም