የአዕምሮ ሕመምን በሚመለከት የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመቀየር ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራን ነው

296

ግንቦት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአዕምሮ ሕመምን በሚመለከት የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመቀየር ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ።

የአዕምሮ ህመም በተፈጥሮም ሆነ በሌላ መንገድ በየትኛውም የእድሜ ክልል ያለን የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ የስነ- አዕምሮ መቃወስ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ለአዕምሮ ሕመም መከሰት በተለይም ስነ-ፍጥረታዊ (አካላዊ)፣ ስነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ መንስኤዎች ዋነኞቹ እንደሆኑም ይጠቀሳል።

ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከአራት ሰው አንዱ በአዕምሮ ሕመም ጤናው ይታወካል፤ ይህ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኢትዮጵያ በብቸኝነት የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሆስፒታል ነው።

በሆስፒታሉ የተመላላሽ ህክምና ማዕከል ዳይሬክተርና የህክምና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ቶሎሳ፤ በአሁኑ ወቅት በአዕምሮ በሽታ መቃወስ ችግር ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ህሙማን ቁጥር መጨመሩንም ገልጸዋል።

በተለይ ከአልኮልና አደንዛዥ እጽ ሱሰኞች መበራከት ጋር ተያይዞ የስነ-አእምሮ ህሙማን ቁጥር ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት፡፡

ከእነዚህ ታካሚዎች መካከልም ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ይህም በተለይ ከሱስ እና አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነት ጋር እንደሚያያዝ አብራርተዋል፡፡

የአእምሮ ህመም እንደሌሎች ህመሞች ሁሉ ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ መዳን የሚችል መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሆስፒታሉ የአዕምሮ ህመምን በሚመለከት የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመቀየር ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የስነ-ልቦና መምህር የሆኑት አቶ በሪሁን በቀለ በበኩላቸው፤የአዕምሮ ህሙማን በሚመለከት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች መኖራቸውን አንስተው፤ይህም ህመምተኞችን ለከፋ ችግር የሚዳርግ ነው ብለዋል፡፡

ህሙማን ከመንፈሳዊው ድጋፍ በተጓዳኝ ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ችግሩን መቀነስ እንደሚቻልም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም