ብልጽግና ፓርቲ አመራሩ ከግለኝነትና ጥቅመኝነት ተላቆ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መፋጠን እንዲተጋ አሳሰበ

240

ሀዋሳ፣ ግንቦት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) አመራሩ ከግለኝነትና ጥቅመኝነት ተላቆ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መፋጠን እንዲተጋ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ አሳሰቡ።

‘አዲስ ፖለቲካዊ እይታ፤ አዲስ አገራዊ እመርታ' በሚል መሪ ሀሳብ የፓርቲው የመጀመሪያ ዙር ክልል አቀፍ የአመራሮች ስልጠና ዛሬ ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በስልጠና መድረኩ ላይ አቶ አብርሃም እንዳስታወቁት፤ ፓርቲው በ1ኛ ጉባኤው ያሳለፋቸውን ታላላቅ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ወደ ህዝቡ በማውረድ በብቃት ተፈጻሚ ማድረግ ከአመራሩ ይጠበቃል።

ለዚህም በየደረጃው ብቁ አመራርና ሙያተኛ ማፍራት በማስፈለጉ ስልጠናው መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

አንድነቱን የጠበቀ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እየተደረገ ያለውን እንቅሰቃሴ ለማጠናከር ስልጠናው ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

ስልጠናው ሀገሪቱ ካጋጠማት ተግዳሮት የሚያሻግር አቅም ለመፍጠር መሰናዳቱን አስረድተው፤ አንዱ ችግር እየፈጠረ ያለው የአስተሳሰብ ብልሽት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከግል ፍላጎትና ጥቅም ባለፈ ለህዝብ ጥቅም የሚቆም አመራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

አመራሩ ይህንን ቁመና በመላበስ ሀገረ መንግስትና ብሄረ መንግሥት ግንባታው እንዲፋጠን በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የስልጠናው ዓላማ ፓርቲው በጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን በብቃት የሚያስፈጽም የአመራር አቅም መገንባት መሆኑን ጠቁመው፤ በመድረኩ ላይ የተለያየ ይዘት ያላቸው ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደርግ ተናግረዋል።

 ለስድስት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና በሁለት ዙር ተከፍሎ የሚሰጥ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ከ30 ወረዳዎችና እና ሰባት ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከክልል ማእከል የተውጣጡ 1 ሺህ 280 አመራሮች መሳተፋቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም