የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያስመዘገበው ድል መላው ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ነው– ሌተናል ጀነራል ሰለሞን

134

ወልዲያ ግንቦት 14/2014 (ኢዜአ)… ”መስዋትነት ከፍላችሁ ሀገርንና ህዝብን ከአሸባሪው ቡድን ወረራ መታደጋችሁ መላው ኢትዮጵያውያንን ያኮራ የተጋድሎ ድል ነው” ሲሉ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰሎሞን ኢተፋ ገለፁ።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ83ኛ ክፍለ ጦር በጦርነቱ የላቀ ግዳጅ ለፈፀሙ የሠራዊት አባላት የማዕረግ ዕድገት አሰጣጥ ሥነሥርዓት በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ዛሬ ተሰጥቷል።

የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰሎሞን ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት ሀገርን የማፍረስ እኩይ ድርጊት በጀግናው ሠራዊታችን ተጋድሎ ተመክቶና አፍሮ እንዲመለስ ተደርጓል።

”ሀገርን የማዳን ተልዕኮ አንግባችሁ አሸባሪውን ቡድን በመመከት ባደረጋችሁት ተጋድሎና ባስመዘገባችሁት  አኩሪ ድል መላው ኢትዮጵያውያን ኮርተውባችኋል” ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ከአሁን ቀደሙ የበለጠ በቀጣይ ተግባሩ አኩሪ ድል ለመፈጸም መትጋት እንደሚገባው ገልፀዋል።

የማዕረግ እድገት ያገኙትን የሠራዊት አባላት እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ዋና አዛዡ ማዕረጉ ለበለጠ ወኔና ድል የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀገር ህልውናን በማስከበር ዘመቻው የ83ኛ ክፍለ ጦር በተሰጠው የግዳጅ ቀጠና ሁሉ አኩሪ ገድል መፈጸሙን በደቡብ ዕዝ የ203ኛ ኮር ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ነገሪ ቶሊና ገልጸዋል።

“ይህ ጀግና ሠራዊት ወደ መሀል ሀገር ለመሻገርና የሚሌን መተላለፊያ መንገድ ለመቁረጥ የሞከረውን አሸባሪውን ቡድን ድባቅ የመታ አኩሪ ሠራዊት ነው” ብለዋል።

“ከቀደመው ጥፋቱ ያልተማረው ቡድን አሁንም ለዳግም ወረራ እያቅራራ በመሆኑ ሀገርን ከመፍረስና ህዝብን ከስቃይ ለመታደግ ይህ ጀግና ሠራዊት ለላቀ ግዳጅ በአዲስ መንፈስ ዝግጁ መሆን አለበት” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የመቶ አለቃነት የማዕረግ ዕድገት ያገኙት ውባለም ተገኘ በሰጡት አስተያየት “ክፍለ ጦራችን ሀገር አፍራሽንና ሰላምን የሚያውክ ጠላትን አሳፍሮ በመመለስ የፈፀመው አኩሪ ገድል መቼም ቢሆን አይረሳም” ብለዋል።

ሠራዊቱ በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻው ወቅት በፈፀመው ጀግንነትና ቁመና ላይ የሚገኝ ታላቅ የሀገር ኩራት መሆኑን ጠቅሰው፤ የማዕረግ እድገቱ ለበለጠ የግዳጅ አፈፃፀም እንድንዘጋጅ አነሳስቶኛል” ብለዋል።

‘የማዕረግ እድገቱ ከአሁን በፊት በተለያዩ ግንባሮች ያገኘነውን አንጸባራቂ ድል አሁንም ለመድገም ይበልጥ ያነሳሳ ነው ያሉት ደግሞ የሻምበልነት ማዕረግ ያገኙት ጉዲሳ ብዙአየሁ ናቸው።

“የሽብር ቡድኑ ዳግም ወረራ ቢፈፅም መላው የሠራዊቱ አባላት በታላቅ የአሸናፊነትና የጀግንነት ሞራል ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

በ83ኛ ክፍለ ጦር አባላት ለሌተናል ጀነራል ሰሎሞን ኢተፋ በጦርነቱ ወቅት ላበረከቱት የላቀ አመራር  የዋንጫ ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን በዝግጅቱ ከፍተኛ መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡