የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት አደነቀ

111

ግንቦት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የኢትዮጵያ መንግስት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት አደነቀ፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂባር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላም እጦትና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ለአብነትም በርካታ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ትግራይ ክልል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረው፤ ይህም በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

"ከሁለት ቀን በፊት 130 የጭነት ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ አቅርቦት ጭነው እንዲሄዱ አድርገናል፡፡ አሁን ደግሞ 200 የሚጠጉ ከባድ የጭነት መኪኖችን አዘጋጅተናል" በማለት ገልጸው፤ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሁኔታዎች ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

May be an image of road

በሳምንቱ 42 የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ 13 የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት፣ 12 የአጋር ድርጅቶች ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 6 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ከአፋር ክልል ወደ ትግራይ ጉዞ መጀመራቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ አቅርቦቱ ያለምንም መስተጓጎል ተደራሽ እንዲሆን የወሰደውን ቁርጠኝነት አድንቀው፤ ይህም ድጋፉ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ማገዙን አስረድተዋል፡፡

የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት ጥናት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ በዋናነት ለአሸባሪው ህወሃት አመራሮችና ተዋጊዎች ተደራሽ እንደሚሆን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት የተጠየቁት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂባር፤ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ አለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት እርዳታ ማከፋፈል ሂደቱ ውስጥ ምንም ሚና እንደሌላቸው ነው የሚገልጹት፡፡

የሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ ሙሉ ለሙሉ ለክልሉ አመራሮች እንደሚሰጥም ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ ካነጋገሯቸው ተፈናቃዮች መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ አቅርቦት ክምችት እየተመናመነ በመምጣቱም፤ በመጪዎቹ የሐምሌና ነሃሴ ወራት ከለጋሽ ድርጅቶች ተጨማሪ ድጋፍ ካልተገኘ ችግሩ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ቀውስ እና በድርቅ ምክንያት ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ እንደሚሹ ጠቅሰው፤ በመሆኑም ለጋሽ አካላት ለእለት ደራሽ የሚሰጡትን ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅርቡ እንደገለፀው፤ መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የገባውን ቃል በማክበር እየሰራ ነው።

ለጋሽ ድርጅቶች ከዚህ በፊት ሰብዓዊ ድጋፍ በመጫን ወደ ትግራይ ገብተው ሳይመለሱ የቀሩ 1 ሺ 25 መኪኖችን ለማስመለስ ግፊት እንዲያደርጉና ወራሪው ኃይል የሚያሰራጨውን ፕሮፓጋንዳ እንዲያቆም ጫና እንዲያሳድሩም መንግስት ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም