የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የአፋር ህዝብ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ምርምር ኢንስቲትዩትን ለማጠናከር እየሰራ ነው

91

ሠመራ፣ ግንቦት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የአፋር ህዝብ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ምርምር ኢንስቲትዩትን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር  መሀመድ ኡስማን ገለጹ።

ከመደበኛው የመማር ማስተማር ስራዎች በተጎዳኝ የክልሉን ህዝብ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ለማልማት እየተሰራ እንደሆነ ለኢዜአ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን የአፋርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የአፋር ህዝብ ባህልና ሀገር በቀል እውቀቶች ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት በዚህ ዓመት አጋማሽ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

ይህም የክልሉን ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ተያያዥ ሀገር በቀል እውቀቶችና ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች በጥናትና ምርምር ታግዞ በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

በታዋቂው የአፋር ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ በነበሩት ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር ሬዶ ስም የተሰየመው የኢንስቲትዩቱ ህንጻ ለሙዚየምነት በሚሆን አግባብ የማስተካከል ስራዎች እየተፋጠኑ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የአፋር ተወላጆችና የአፋር ወዳጆች በእጃቸው የሚገኙ ቅርሶችን ለዩኒቨርሲቲው እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።