ሰላም፣ ፀጥታና ልማትን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን ተሰልፈን የድርሻችንን እንወጣለን – ወጣቶች

104

ፍቼ ግንቦት 14/2014/ኢዜአ/— በመሰዋዕትነት የተገኙ ለውጦችን በመጠበቅ ሰላም፣ ፀጥታና ልማትን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የድርሻቸውን እንደሚወጡ በፍቼ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ ወጣቶች አመለከቱ ፡፡

በዞኑ ፍቼ ከተማና አካባቢው የተውጣጡ 1 ሺህ 500 የሚጠጉ ወጣቶች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬ በፍቼ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የሰላም ኮንፈረንሱ ተሳታፊ ወጣቶች አሸባሪው የሸኔ ቡድን በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ከመንግስት ጎን ተሰልፈው እንደሚታገሉም አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም በመራር ትግልና መሰዋዕትነት የተገኙ የለውጥ ትሩፋቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የአካባቢያቸውን ሰላም፤ ፀጥታና ልማት ለማስቀጠል በሚደረገው ትግል ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ባወጡት ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ  ጠቁመዋል፡፡

ድህነትና ኋላቀርነትን ለማስወገድ ስራን ሳይንቁ  በመስራት  የሃገሪቱን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን እንደሚጥሩም በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

ከተሳታፊ ወጣቶች መካከል ወጣት ተፈሪ ማሾ እንዳለው በወጣቶች ትግልና መሰዋትነት የተገኘው ለውጥ ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራ ከመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢውንሰላምና ፀጥታ  እንደሚጠብቅ ጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የእድሜ አቻዎቹ  ከሸኔ ቡድን ርካሽ ዓላማ እንዲርቁ የበኩሉን ምክር እንደሚሰጥም  በውይይቱ  ላይ ገልጿል፡፡

የዞኑ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሽመልስ ጣፋ የኦሮሞ ህዝብ በጀግንነት፤ በአብሮነትና በአቃፊነት የሚታወቅ መሆኑን አስታውሶ ይህንን ለማጠልሸትና ከሌሎች ጋር ለማጋጨት የሚሰሩ ሃይሎችን በቁርጠኝነት እንደሚታገል ተናግሯል፡፡

የፍቼ ከተማ ምክትል ከንቲባ  አቶ ሙሐመድ ጉዬ በበኩላቸው በሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ወጣቶች  የጎላ  ትግልና መሰዋትነት የከፈሉ መሆኑን ጠቁመው  አሁንም የሀገር ሠላም፣ ልማትና እድገት እንዲፋጠን ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ተወካይ ወይዘሮ መዝገቤ አበበ እንዳሉት ወጣቶች የለውጥ ሃዋሪያ እንደሆኑ ሁሉ  በሀገርና አካባቢ ሰላምና ፀጥታ ላይ እንቅፋት የሆኑ ቡድኖችን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥም የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

አካባቢያቸውንም ከድህነት ለማውጣት በእርሻ፤ በእርባታና ሌሎች አገልግሎቶች በንቃት በመሰማራት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ለሰላም፤ ለጋራ መግባባትና አብሮነት ያለውን ፍላጎት በሚመጥን ደረጃ ወጣቶች አርአያነት ያለው  ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

በዞኑ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢነት በተዘጋጀው በዚሁ ኮንፈረንስ በሰላም ግንባታ፤ በግጭት መካላከልና ማስወገድ፤ በሰብዓዊ መብትና አያያዝ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡