በአርሲ ዞን በመጪው የመኸር ወቅት በኩታ ገጠም ስንዴ በስፋት ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል- የዞኑ አስተዳደር

84

ግንቦት 14/2014/ኢዜአ/ በአርሲ ዞን በመጪው የመኸር ወቅት በኩታ ገጠም ስንዴ በስፋት ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሙሣ ፍሮ ተናገሩ፡፡

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በቆጂ ከተማ በአርሶ አደሩ መካከል ወንድማማችነትና አብሮነትን ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ የአርሶ አደሮች ፌስቲቫል ተካሄዷል፡፡

በፌስቲቫሉ ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች የታደሙ ሲሆን፤ የዞኑን ባህልና ምርት የሚገልጽ ትርኢት እንዲሁም ባህላዊ ምግቦች ለእይታ ቀርበዋል፡፡

ፌስቲቫሉ በአርሶ አደሮች መካከል ወንድማማችነት፣ አብሮነት እና መተባበርን የሚጠናክር መሆኑም ተገልጿል ።

የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሙሣ ፍሮ፤ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱ አርሶ አደሮቹ ልምዶቻቸውን የሚለዋወጡትበት መድረክ እንዲያገኙ ይረዳል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት እየሰራች ባለችበት  ወቅት ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱ አርሶ አደሩ ለተሻለ ውጤትማነት እንዲሰራ ያግዘዋልም ነው ያሉት።

በዞኑ አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ስንዴ ለማልማት እንዲችል ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ነው ያነሱት፡፡

የአርሲ ዞን ስንዴና ገብስን በኩታ ገጠም በማምረት የሚታወቅ አካባቢ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜያት ውዲህ ደግሞ የመስኖ ልማትን ጨምሮ በስንዴ ምርት ላይ በስፋት ስሙ የሚጠራ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡