የአብሮነትና አንድነት መገለጫ የሆነውን የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

82

ግንቦት 14/2014/ኢዜአ/ የአብሮነትና አንድነት መገለጫ የሆነውን የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡

በሐረሪ ህዝብ ዘንድ በደማቅ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የሸዋል ኢድ ዛሬ በአዲስ አበባ መቻሬ ሜዳ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የሸዋል በዓል የሐረሪ ህዝብ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ጋር በጋራ ሆነው የሚያከብሩት የአብሮነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የዘንድሮው የሸዋል በዓል አንድነትን እና ወንድማማችነትን በሚያሳይ መልኩ መከበሩንም ነው የገለጹት፡፡

የሸዋል ዒድ  ከአስራ አምስት ቀን በፊት በሐረሪ ክልል በድምቀት መከበሩን አስታውሰው ፤ በዓሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  “ከኢድ አስከ ኢድ ወደ በአገር ቤት” ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ  ወገኖች ጋር በጋራ መከበሩን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በአብሮነት መከበሩ የክልሉን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት፡፡

የአብሮነትና አንድነት መገለጫ የሆነውን የሸዋል ኢድ አከባበር በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በበዓሉ ተሳታፊ የሆኑት ዶክተር ፈትሂ ባህሩ በበኩላቸው የሸዋል ኢድ በአዲስ አበባ መከበሩ  የሐረሪን ታሪክ ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ነው የገለጹት፡፡

በመቻሬ ሜዳ በተከናወነው የበዓሉ አከባበር ላይም የሐረሪ ህዝብ መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ቅርሶች፣ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠሩ ሃይማኖታዊ መጽሃፍት እና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ቀርበዋል፡፡