ኀብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመረውን ጥረት ሊደግፍ ይገባል

101

ግንቦት 14/2014/ኢዜአ/ ኀብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመረውን ጥረት ሊደግፍ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነቷና ሉአላዊነቷ ተጠብቆ የኖረች አገር ናት።

ኢትዮጵያዊያን እጅጉን የዳበረና አንደኛው ማሕበረሰብን ከሌላኛው ጋር በጥብቅ የሚያስተሳሰር ባህልና እሴት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውም አይዘነጋም።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ ይህን ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለማፍረስ የውጭና የውስጥ ጠላቶች በተናበበ መልኩ እየሰሩ መሆኑ ይገለጻል፡፡

ይህም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማደፍረስ ባሻገር የአገር ህውናን ን እየተፈታተነ መምጣቱም ይስተዋላል።

በመሆኑም በኢትዮጵያዊያን ዘመን ተሻጋሪ አብሮነት ላይ አደጋ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።

የአገር አንድነትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረትም መንግስት ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።  

ኢዜአ ያነጋገራቸው ወይዘሮ የምስራች ፈለቀ እና አርቲስት ደበበ እሸቱ እንደሚሉት፤ የአገር አንድነትና ህልውናን ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።

በመሆኑም ዜጎች አብሮነታቸውን በማጠናከር ሰላሟ የተጠበቀና አንድነቷም የጠነከረ አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በአገር አንድነት ላይ የህልውና አደጋ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችንም በጋራ መታገል እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

ኀብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የአገር ሉዓላዊነትና የህዝቦች አብሮነት ላይ አደጋ ለመጣል በሚሰሩ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላምና ደህንነት በመንግስት ጥረት ብቻ እንደማይረጋገጥ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ ህብረተሰቡን ለማደናገር የሚለቀቁ መረጃዎችን በመለየት ትክክለኛውን እና ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅመውን ብቻ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የአገርን ስም ለማጥፋት የሚደረጉ ዘመቻዎችንም በጋራ መከላከል ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ ከውጭ የሚሰነዘርንም ሆነ በአገር ውስጥ ሆነው የሚንቀሳቀሱትን በጋራ መመከት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም