በምዕራብ ጉጂ ዞን የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጉጂ ዞን የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው

ዲላ ግንቦት 14/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ድርቅን በመቋቋም ምርታማ መሆን የሚችሉ ከ51 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡዴሳ ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድርቅን በመቋቋምና እርጥበትን በማቆየት ምርታማነትን የሚጨምሩ የችግኝ ዝሪያዎች ተከላ እየተከናወነ ነው።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በዞኑ ተከስቶ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝውን ድርቅ በዘላቂነት መከላከልን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።
በተለይም እንደ ዋርካ፣ ጥድ፣ ቀርከሃ፣ ዝግባ፣ ጥቁር እንጨትና ሌሎች የሀገር በቀልና የውጭ ዝሪያ ያላቸው ከ51 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ተከላ መጀመሩንም ጨምረው ገልጸዋል።
እነዚህ ችግኞች ከ50 በላይ በሚሆኑ የመንግስትና የግል ችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ከተተከሉ ከ30 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ በተደረገው ጥረት 78 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ገልጸዋል።
የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለታለመላቸው ዓላማ እስኪውሉ ድረስም ህብረተሰቡ ክትትልና እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከስምንት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎችን የድርቅ ስጋት በሚስተዋልባቸው በ25 ተፋሰሶች ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግብራ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የቡሌ ሆራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው አሰፋ ናቸው።
በተለይ የክረምቱን ውሃ ለመያዝ የሚያስችሉ የእርከን፣ የጉርጓድና ሌሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ቀደም ብሎ በማከናወን በአሁኑ ወቅት ተከላው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዘመቻውም ከአርሶና አርብቶ አደሩ በተጓዳኝ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የጸጥታ አካላት በስፋት እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሶሬሳ ይገዙ እንዳሉት በአከባቢያቸው የደን ሽፋን እየተመናመነ በመምጣቱ የግብርና ምርታማነት ላይ ጫና ከማሳደሩ በተጨማሪ የድርቅ ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።
በተያዘው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአፈር ለምነትን የሚጨምሩና ለከብቶች መኖ የሚያገለግሉ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ድርቅን ለመከላከል እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ አስፈላጊውን አገልግሎት እስኪሰጡ ድረስ እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።