በሐረሪ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ የጉድጓድ ቁፋሮ በዘመቻ ተጀመረ

166

ሀረር ግንቦት 14/2014(ኢዜአ) … በሐረሪ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሚከናወነው ችግኝ ተከላ የጉድጓድ ቁፋሮ በዘመቻ ተጀመረ።

የችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮውን በኤረር ወረዳ ወልዲያ ቀበሌ ካራ ተራራ ላይ ያስጀመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሆነው ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የካራ ተራራ በደን ምንጣሮ የተራቆተ መሆኑን በመጥቀስ በዘመቻው ተራራው በደን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ተራራው በመራቆቱ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ጎርፍ እየፈጠረ አፈሩን ከመሸርሸሩ ባሻገር አርሶ አደሩን ለችግር ይዳርግ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በዘመቻው የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም የዝናብ ውሃውን በመሬት ውስጥ ለማቆየት ከጉድጓድ ቁፋሮው በተጨማሪ በእርከን ስራና መሬቱን በማሰር የአፈር መሸርሸሩን ለመከላከል ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሯ አክለውም በክልሉ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በዝግጅት ላይ እንደሚገኙና በኤረር ወረዳ ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልፀዋል።

የኤረር ወረዳ ወልዲያ ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው የካራ ተራራ በከፍተኛ ሁኔታ በመራቆቱ ዝናብ በሚጥልበት ግዜ አፈሩን እያጠበ ውሃውንም ሳይጠቀሙበት ያልፍ እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን ላይ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝናብ በሚጥልበት ግዜ አፈሩን ከመሸርሸር እንደሚከላከልላቸው ገልፀው ለችግኝ ተከላው አስፈላጊውን የጉድጓድ ዝግጅት በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ችግኞች በብዛት ከተተከሉ የአየር ንብረት ፀባዩም ይስተካከላል፤ ውሃውም አፈሩን ሸርሽሮ እንዳይሄድ ያደርጋል ብለዋል አርሶ አደሮቹ፡፡

በመሆኑም በተራራው ላይ ውሃ እንዲያቁር “የጉድጓድ ቁፋሮና የእርከን ስራ በማከናወን ላይ እንገኛለን፤ ችግኞቹ ለፍሬ እስኪበቁ ድረስም አስፈላጊውን እንክብካቤ እናደርጋለን” ብለዋል።

በጉድጓድ ቁፋሮ ዘመቻው ላይ በርካታ የኤረር ወረዳ ወልዲያ ቀበሌ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል።

በዘመቻው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ ተገልጿል።