በክልሉ እየተካሄደ ያለው የአትልክትና ፍራፍሬ ልማት ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው

117

ሀዋሳ ግንቦት 14/2014(ኢዜአ)…. በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተገኙ ውጤቶች በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት የሚያግዙ መሆናቸውን በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች በተለያዩ ዞኖች በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች እየተከናወኑ ያሉ የጥምር ግብርና ልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው።

በቡታጅራ ማዕከል ሲሰለጥኑ የነበሩት የብልፅግና ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች እየለማ ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመጎብኘት ላይ ናቸው።

የዞኑ አርሶ አደሮች በተለይ አቮካዶ በማልማት ወደ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።

በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ እየተካሄደ ባለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።

የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱን በአግባቡና በተጠናከረ መልኩ ከተያዘ በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

በተለይም በግንባር ቀደም(ሞዴል) አርሶ አደሮች ማሳ እየተካሄደ ያለው የግብርና ስራ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።

በየደረጃው እየተካሄደ ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት  የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የክልሉ ማህበረሰብ በተለያዩ የግብርና ልማት ዘርፎች እያካሄደ ያለው የልማት ስራ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉ አመራሮች ይህን የግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ልምድ በመቀመር በየአካባቢያቸው እንደያሰፉ አሳስበዋል።

በሞዴል አርሶ አደሮች የተጀመረው  የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ወደ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ ተሞክሮን የማስፋት ስራ በትኩረት መስራት ይገባልም ብለዋል።

በክልሉ በቡታጅራ፣ ሆሳዕና፣ አርባምንጭና ወላይታ ሶዶ ከተማ በአራት ማዕከላት ሰሞኑን በስልጠና ላይ የነበሩ የብልፅግና ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች በሞዴል አርሶ አደሮች እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ስራዎችን ተሞክሮ እየተመለከቱ ነው ።