የኢትዮጵያ የ2010 ጉዞ ሲቃኝ

137
ምህረት አንዱዓለም/ኢዜአ/:- 2010 ዓ.ም ሊጠናቀቅ ቀናት ቀርተውታል። ለመሆኑ በዓመቱ በኢትዮጵያ ምን ምን ክስተቶች ነበሩ፤ አምና መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ሲጀመር "ዓመቱ የኢትዮጵያ ከፍታ ነው" የሚል መልዕክት ተነግቦ ከህጻናት እስከ አዛውንት ከመንግስት ተቋማት እስከ ሃይማኖት ተቋማት ተደጋግሞ ሲነሳ እነደነበር እናስታውሳለን። 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቆጣጠሩ ታሪክ እየተወ ሲያልፍ በሀገሪቱ የተለያዩ ክስተቶች ተስተውለዋል፤ ደስ የሚሉ ታሪኮች ተፈፅመዋል፤ የሚያስቆዝሙና የሚያስደነግጡ ክስተቶችም እንዲሁ። ከዜጎች ሞትና መፈናቀል እስከ አስደሳች የለውጥ ጉዞ ኢትዮጵያ በ2010 ብዙ የታሪክ ገጾችን በጊዜ መጽሃፍ ላይ አትማለች። በሀገሪቱ ምን ክስተቶች ተስተዋሉ ? በ2010 እንዲህ ሆነ፤ በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ በሚባል ደረጃ በተወሰኑ አካባቢዎች የማይረሱ ጉዳቶችን ያስከተሉ ግጭቶች፣ ብጥብጦች ነበሩ፤ ዜጎች በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸው እየተለዩ እንዲጠቁ የተቀነባበሩ ሴራዎችም ተሞክረው ከሽፈዋል፡፡ ብጥብጦቹ ቀጣናዊ ትርምስ መፍጠርን ዓላማ ያደረጉ እንደነበሩም በመንግስት ደረጃ መገለጹ ይታወሳል፤ ብዙዎች ለሞት ሲዳረጉ፣ በሚሊየን የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል፤ ብዙዎች መጠለያ አልባ ሆነው የመንግስትን ድጋፍ በመጠበቅ ላይ ናቸው፣ እናት ሀገር ኢትዮጵያ በጥቅመኛ አጋፋሪዎችና ነገር ጠንሳሾች ነገር የተጠነሰሰበት በአንጻራዊነትም የከሸፈበት ዓመት አሳልፋለች። የከፍተኛ ትምህርት መካናት(ዩኒቨርሲቲዎችም) ለተወሰኑ ጊዜያት በትምህርት ማቆም አድማ የተመቱበትን ጊዜ አንዘነጋውም፤ ሌላው አጋጣሚ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሞያሌ ላይ በስህተት 9 ሰላማዊ ዜጎችን የገደሉበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የሚመሩት መንግስት የጀመራቸውን ለውጦች ለመደገፍና ለመደመር ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም  ከ4 ሚሊየን በላይ ህዝብ በመስቀል አደባባይ በታደሙበት የቦምብ ጥቃት ተከሰተ፤ በዚህም አራት ሰዎች ሲሞቱ ከ150 በላይ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሲጀመር አስደሳች የነበረው ድባብ አጨራረሱ አሳዛኝ ሆኖ በሀዘን ብዕር ታትሞ አልፏል። የኢፌድሪ አየር ሃይል አውሮፕላን ከድሬዳዋ ወደ ቢሾፍቱ ሲበር ተከስክሶ 17 ሰዎች ያለቁበት ጊዜም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጦችን በመደበኛ የህግ ስርዓት ማስከበር አልተቻለም በሚል ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ   አዋጅ አወጣ፤ አዋጁ ጸንቶ የሚቆይበት ጊዜ ሳያልቅ ግንቦት ወር ላይ ተነሳ። ዓመቱ የብስራት ዜናዎች ከኢትዮጵያ ማዕከል እስከ አጽናፍ የተስተጋባበት ነበር፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈሚ ኮሚቴ በታህሳስ ወር ለ17 ተከታታይ ቀናት ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት ወስዶ አገሪቷን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከልም፤ የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እስረኞችን በምህረት፣ በይቅርታና ክስ በማቋረጥ እንዲፈቱ አድርጓል። በዚህም የዋልድባ መነኮሳት፣ እነ ዶክተር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ በፌደራልና በክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎችና እሰረኞች ተፈትተዋል። መንግስት በምህረት የሚፈቱትን በተመለከተም የምህረት አሰጣጥ ስነስርዓት አዋጅ ማውጣቱና ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩም በ2010 ዓ.ም ያየነው መልካም ተግባር ነው። የአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት አመራር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በልዩ ሁኔታ እንዲፈቱ የተደረጉበት ክስተትም ይታወሳል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢህአዴግና መንግስት ለጀመሩት የለውጥ አካል መሆን አለብኝ ብለው ከአመራርነት በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውም ሌላው በዓመቱ የታየ ክስተት  ሲሆን፤የአቶ ኃይለማርያም ውሳኔም በሳልነት የታየበት መሆኑ በብዙዎች ተነግሯል፤ መንግስትም በአመራርነት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሸልሟቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ኢህአዴግ ባካሄደው ስብሰባ ዶክተር ዐቢይ አህመድን በአቶ ሃይለማርያም ምትክ የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ በመሾም  መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ዶክተር ዐቢይን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ። ዶክተር ዐቢይም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ መንግስት ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑን የሚያሳዩ በሳል ንግግሮችን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አደረጉ። ‹‹ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን›› በሚለው ንግግራቸውና በሌሎችም አገራዊ አንድነት እንዲፈጠር በሚያስተጋቡ መልዕክቶቻቸው የመላውን ኢትዮጵያውያንን ቀልብ መግዛት ችለዋል፡፡ ምን መልካም ነገሮችና ስኬቶች ተመዘገቡ ? በዓመቱ ከተፈጸሙት መልካም ነገሮች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ ጋር የሰላም ግንኙነት ለመጀመር ዝግጁነት መኖሩን ይፋ ማድረጋቸው ነው፤ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂም  በውጭ ጉዳይ ሚነስትር ኦስማን ሳልህና በፕሬዚዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ የሚመራ ልዑክ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ልከዋል። በኢትዮጵያም ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም በሃምሌ ወር መጀመሪያ ወደ አስመራ ጉዞ አደረጉ፤ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በፈገግታ ተቀበሏቸው፤ ሁለቱ መሪዎች የኢትዮጵያንና የኤርትራን ህዝብ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በእርስ በእርስ ትስስስር የሚጠቅም አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትም ተፈራረሙ፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ከ22 ዓመታት የቅራኔ ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ገቡ፤ የኤርትራ ኤምባሲም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኤምባሲም በአስመራ ዳግም ተከፈቱ፤ የአትዮጵያና የኤርትራ አየር መንገዶችም ወደ አስመራና ወደ አዲስ አበባ በረራ ጀመሩ፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሃያ ዓመታት የዘለቀውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አገላለፅ ‹‹ሞት አልባው›› የተባለው ጦርነት እንዲያበቃ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት በገቡት ቃል መሰረት ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ አመራር ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንደምትቀበል በማሳወቅ ሰላም እንዲሰፍን ወሳኙን ሚና ተጫውተዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም እንዲመጡ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ለፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ ማበርክታቸውም በ2010 ዓ.ም የክስተት ገጽ ላይ የተጻፈ ሁነት ነው። መቀሌ ተብላ የምትጠራው የኢትዮጵያ የንግድ መርከብም ከ20 ዓመታት በኋላ ከምጽዋ ወደብ ዚንክ ጭና ወደ ቻይና ያቀናችበት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈው በዚሁ ዓመት ነው። ለ26 ዓመታት ‹‹የውጭና የአገር ውስጥ›› በሚል ለሁለት ተከፍሎ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ከነበረው የመከፋፈል አባዜ ወጥቶ በእርቅ በአንድ ሲኖዶስ መመራት ጀምራለች፤ በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩት አራተኛው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆርዮስም ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፤ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤትና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መካከል ላለው አለመግባባት ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ እርቅ ማውረዱም በ2010 ዓ.ም ከተሰሙ የደስታ ዜናዎች አንዱ ነበር። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴን በማወያየት በመካከላቸው የነበረው ችግር እንዲፈታ ተደርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በሽብር ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎችን ጨምሮ በትጥቅ ትግልና በሰላማዊ መንገድ ለተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎችም ይፋዊ ጥሪ በማድረግ በሀገራቸው ውስጥ ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲጀምሩ መንግስት በጽኑ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአሸባሪነት ፈርጇቸው የነበሩትን ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና ኦብነግ ከአሸባሪነት ዝርዝር የሰረዘውም በዚሁ ዓመት ነበር። የመንግስትን ጥሪ እና በሀገሪቱ ያለውን የለውጥ ተስፋ ተከትሎ ግንቦት ሰባት፣ አዴሃን፣ ኦብነግ፣ ኦነግ የትጥቅ ትግላቸውን አቁመው ወደ ሀገር በመግባት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸውን አሳወቁ፤ ልዑኮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከመንግስት ጋር ውይይት ከጀመሩት መካከል፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የአሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ሌሎችም ይገኙበታል። እየሸኘነው ያለው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የኢትዮጵያውያንን ልብ በሀሴት የሚሞላ የይቅርታና የፍቅር እሴታቸውን መርጨት የጀመሩበት ዓመትም ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ግፊትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራቸው የወጡ ኢትዮጵያውያን ወደ እናት ሀገራቸው እንዲመለሱ ባደረጉት ጥሪ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) መስራችና አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ፣ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና አርቲስት ታማኝ በየነ እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችም የእምዬ ኢትዮጵያን አፈር የረገጡበት የአየሯን መዓዛ ያሸተቱት በዚሁ በ2010 ዓ.ም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት አገራት ፣ከግብፅና ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ መሰረት ያደረገውን ግንኙነት ለማስቀጠል የሚረዳ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ከጂቡቲ እስከ ኡጋንዳ፣ ከአስመራ እስከ ግብጽ ቀጠናውን በዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ያካለሉበት፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ሩቅ ምስራቅ፣ እንዲሁም እስከ ሰሜን አሜሪካ ስኬታማ የሚባል የዲፕሎማሲ ጉዞ ያደረጉበት ዓመትም ሆኖ አልፏል። ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በጎረቤት አገሮች በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ቅራኔ እንዲፈታ በአሸማጋይነት በመስራት  ውጤት ያስገኘችበት ዓመትም ነው፡፡ በአሜሪካ ሦስት ከተሞች ‹‹ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ›› በሚል መሪ መልዕክት ባደረጉት ጉብኝት ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ያደረጉበት ዓመት፥ መንግስትና ዲያስፖራው በግልጽ ተቀራርበው ሀገራቸውን ስለመጥቀም የተወያዩበት ጊዜም በሃምሌ ጀንበር የታሪክ ምዕራፍ ተመዝግቦ አልፏል፤ ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲና ሎስ አንጀለስ ከተሞችን የረገጡባቸው ቀናትም በየዓመቱ የኢትዮጵያውያን ቀን ሆነው እንዲከበሩ በከንቲባዎቻቸው አማካይነት መወሰናቸውም ይታወሳል። ከሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ አገሪቱ የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ማውጣት እንደምትጀምር ዶክተር ዐቢይ አብስረዋል፡፡ እረፍት አልባው የሀገር መሪ ዶክተር ዐቢይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤመሬቶች፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ጂቡቲ ባቀኑበት ወቅት ከመሪዎቹ ጋር በመግባባት “ከምንም ነገር በፊት ዜጎቻችን ይበልጡብናል፤ ቅድሚያ ዜጎቻችንን ልቀቁልን” በሚለው መርሃቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲፈቱና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን በብዙዎች አድናቆት የተቸረው ተግባር ሆኖ ተሸኝቷል። በሳዑዲ ቆይታቸው በህክምና ስህተት ለ12 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ የቆየው ታዳጊ አብዱልአዚዝ በሳዑዲ ካሳ እንዲከፈለውና ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ እስከ ማድረግ የደረሰ በጎ ተግባር የፈጸሙበት ዓመትም ነው 2010 ዓ.ም። ኢትዮጵያዊው ባለሃብት ሼክ መሃመድ አሊ አል አሙዲ በሳዑዲ ወደ እስር የገቡበት እና ከዛሬ ነገ ይፈታሉ በሚል ዓመቱ በጉጉት የተጠናቀቀበት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከራሳቸው ጀምሮ የሚመሩት መንግስት አመራር እያስተባበረ ዓመቱ የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የመደመርና የበጎ አድራጎት ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዘመቻ ያስጀመሩበት ዓመት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመዲናዋ ለ208 ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ያበረከቱበት፣ ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና ሌሎች አመራሮች ገር ሆነው የእማሆይ አዱኛን ደሳሳ ጎጆ ያደሱበት፣ ከ1 ሽህ ለሚበልጡ በጎ አድራጊ ወጣቶች ሀገራዊ ስምሪት የሰጡበት በጎ ሀሳብና ተግባርም በብዙዎች ልብ ታትሞ በታሪክነት አልፏል። ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ መንግስቱን እንዲጎበኙ የተደረገበት ዓመትም ነበር፡፡ በዓመቱ በጎ ተግባር ፈጽመዋል የተባሉት የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳም የስድስተኛው የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፤ በዓመቱ ከመምህርነት ዘርፍ መምህር ስመኘው መብራቱ፣ ከመንግስታዊ ኃላፊነት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከበጎ አድራጎት ዘርፍ አቶ መኮንን ሙላት፣ ከሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ጋዜጠኛ ፀጋዬ ታደሰ (ፀጋዬ ሮይተርስ)፣ ከቅርስና ባህል ዘርፍ ዳግማዊ ላሊበላን የሰሩ አባ ገብረመስቀል ተሰማ፣ ከንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ የአዲስ አበባው የተቻለ ጋራዥ ባለቤት አቶ ተቻለ ኃይሌ፣ ከኪነጥበብ ዘርፍ ለብዙ ድምፃውያን ዜማና ግጥም በመድረስ የሰጠው አበበ ብርሃኔ፣ ከሳይንስና ምርምር ዘርፍ ፕሮፌሰር ሽብሩ የበጎ ሰው የዋንጫና የምስክር ወረቀት የተሸለሙበት ነው። በዓመቱ ምን ምን ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተላልፈው ነበር ? ኦህዴድ ዶክተር ዐቢይ አህመድን ሊቀመንበር፣ አቶ ለማ መገርሳን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የሾመበት ውሳኔ ይታወሳል፤ በሀገሪቱ አሁን ያለውን ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ ያገናዘበ የድርጅት ስያሜ፣ አርማና የመዝሙር ለውጥ ለማድረግ ወስኗል፤ በኢህአዴግ ምክር ቤት የሚወክሉትን በርካታ አባላት በማንሳትም አዳዲሶችን ተክቷል፤ ለአመራር አይመጥኑም  ያላቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ከማስጠንቀቂያ እስከ ማገድ  እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል። ብአዴን የአማራ ብሔርተኝነት የሞት የሽረት ትግሌ ነው መሰረቴም እሱ ነው ማለቱ ይታወሳል፤ የንቅናቄው የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንቦች እንዲሻሻሉና አርማውም ህዝቡን ከግምት ያስገባ እንዲሆን አሻሽላለሁ የሚል ውሳኔ ያሳለፈው በዚሁ ዓመት ነው፤ ጥረት ኮርፖሬትና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት እንዲሆን፥ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ያለው የተዛባ ውሳኔ በአስቸኳይ በፌደራል መንግስቱ ውሳኔ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቋል፤ ከጥረት ኮርፖሬት ብልሹ አሰራር ጋር በተገናኘ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ማገዱም በ2010 የተሰማ ዜና ነው። ደኢህዴን የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ቀይሯል፤ የህዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ከሊቀመንበርነት በለቀቁት አቶ ሺፈራው ሽጉጤ ምትክ ሲሾሙ፣ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ደግሞ በአቶ ሲራጅ ፈጌሳ ቦታ የንቅናቄው ሊቀመንበር ሆነዋል። የደቡብ ክልል ህዝቦችን የሚመጥን የአመራር ለውጥ ማድረጉም ይታወቃል። ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሃት/ ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ከማእከላዊ ከሚቴ አባልነት በማገድ፣ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤልን ሊቀመንበርና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአበሔርን ደግሞ ምክትል አድርጎ መሾሙ የታወሳል። ኢሶህዴፓ፣ ቤጉዴፓ፣ አፍዴፓ፣ ጋህአዴንና የሀረር ብሔራዊ ሊግ(ሀብሊ) የተሰኙት የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችም በ2010 ዓ.ም በድርጅቶቻቸው ውስጥ ህዝባዊነት እንዲቀድም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸው አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ከ16 በላይ ሚኒስትሮችን፣ በርካታ ሚኒስትር ዲኤታዎችን፣ የጸጥታ መስሪያ ቤት ሃላፊዎችን የሾሙበትና የተቋማት አደረጃጀት እንዲቀየር ያደረጉበት ክስተትም ይጠቀሳል። ኢህአዴግ በዚህ ዓመት ባካሄዳቸው ስብሰባዎቹ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዲጠናከር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ በፖለቲካ አቋማቸው የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ መወሰኑ ይታወቃል፤ ኢህአዴግ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል አልጀርስ ላይ የተፈረመውን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር መወሰኑን ያረጋገጠበት ዓመትም ነው። ብዙዎችን ያነጋገረው እንደ ኢትየጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌ እና ባህር ትራንስፖርት የመሳሰሉ ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል እንዲዛወሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሃሳቦች ውሳኔ መስጠቱም የዚህ ዓመት ክንውን ነው። መንግስት የካቢኔ የስብሰባ ቀን ቅዳሜ እንዲሆን ማድረጉ፣ በእስረኞች አንደበት እንደተገለጸው የስቃይ ምርመራ የሚካሄድበት ማዕከላዊ መዘጋቱ፣ የዚህ ዓመት ድንቅ ውሳኔዎች ናቸው። የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም ከመፈራት ይልቅ በስራዬ መከበር ላይ አተኩራለሁ፤ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ርቄ ለመስራት ወስኛለሁ ማለቱም በዚሁ ዓመት የተጻፈ ክስተት ነው፣ ለበርካታ ዓመታት የት እንዳለ እንኳ የማይታወቀው መስሪያ ቤት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲጎበኝ ተደርጓል፤ የመከላከያ ሰራዊትን ለበርካታ ዓመታት የመሩት ጀኔራል ሳሞራ የኑስ የክብር ኒሻን ተሸልመው ሲሰናበቱ፤ ጀኔራል ሰዓረ መኮንን የሰራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው መሾማቸውም የ2010 ዓ.ም ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል። አዲስ አበባ በሶስት ምክትል ከንቲባዎች መመራት የጀመረችው፣ ከከተማ እስክ ክፍለ ከተማ አመራሮችን በነባራዊ ሁኔታ የለወጠችበት ዓመትም ነው፤ ከተማዋ በየወሩ የመጨረሻው ቅዳሜ የሚከናወን የጽዳት ዘመቻ “እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ እናንተስ” በሚል መሪ ሃሳብ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የጀመረችው በዚሁ በ2010 ዓ.ም ነው። በ2010 ዓ.ም የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ ክስተቶችስ ምን ነበሩ?  ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ የውጭ መንግስታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አፋቸውን ሞልተው የእድገት ጉዞዋን ለመደገፍ ቃል እንዲገቡ፣ እንደ ተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ያሉ ሀገራትም በልዩ ልዩ መስክ የሚተገበር የ3 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ ያደረገችበት ዓመት ነው፤ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ ቢያንስ አንድ ዶላር ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡበት እና የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋቁሞ ወደ  ስራ በመግባት የሸኘነው ዓመት ነው። የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘቦች በእጃቸው የሚገኝ ግለሰቦችም ወደ ባንክ በመውሰድ እንዲመነዝሩ በሰጡት ማሳሰቢያ መሰረት በሚሊየን የሚቆጠር የውጭ ሀገራት ገንዘብ ወደ ባንኮች ለምንዛሬ የጎረፈበት፣ በየቤቱ በካዝና ተቆልፎ የነበረ ገንዘብ የባንኮችን ደጅ የረገጠበት፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ሊወጣ ሲል እጅግ ብዙ ገንዘብ በቁጥጥር ስር የዋለበት ዓመትም ነው 2010 ዓ.ም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል ፤በዚህም የአገር ውስጥ የግል ባንኮች ከብሄራዊ ባንክ ለሚገዙት ቦንድ ያገኙት የነበረው የሶስት በመቶ ወለድ ወደ አምስት በመቶ እንዲያድግ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡት የ50 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገደብ እንዲነሳ፣ የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን 30 በመቶ ለብሄራዊ ባንክ የሚሸጡበት ተመን በመግዢያና በመሸጫ መካከል ባለ (አማካይ) ዋጋ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ክፍያ እንዲቀበሉ የተፈቀደላቸው የንግድ ድርጅቶች በስራ ላይ ካለው ዝርዝር በተጨማሪ:- በኤርፖርት ውስጥ የሚሰጥ የቴሌኮም አገልግሎት፣ ለውጭ ቱሪስቶች የቻርተርድ አገልግሎት የሚሰጡ የግል አየር መንገዶች፣ የውጭ ዜጎችን የሚያስተናግዱ የእንግዳ ማረፊያዎች  የውጭ ዜጎችን የሚያስተናግዱ ልዩ ክሊኒኮች እና ሆስፒታሎችን እንዲጨምር በኮሚቴው ተወስኗል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ማነቆ ውስጥ ገብቶ የነበረው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ጥቁር ገበያው ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ጉልህ ለውጥ መጥቷል፡፡ በተለይ ዳያስፖራው ለእናት አገሩ ጥሪ ምላሽ እንዲሰጥ ይፋ ያደረጉት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡ የ2010 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለን፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸውን፣ አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው ፍቃዱ ተክለማርያምን፣ ገጣሚ ሶሎሞን ደሬሳን፣ ድምጻዊ ታምራት ደስታን፣ የወላይታ ቀዳሚ ዘፋኝ ኮይሻ ሴታ፣ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን በሞት የነጠቀን ዓመትም ሆኖ አልፏል። በአጠቃላይ የ2010 ዓ.ም እያንዳንዱ ቀናት በኢትዮያውያን ላይ መጥፎም ጥሩም ገጽታን አሳርፈው አልፈዋል፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ የምንቀበለውን አዲሱን ዓመት ካለፈው መልካምነትን እና ስኬትን ይዘን፣ መጥፎ አጋጣሚዎችን ላለፈው ዓመት ትተን መቀበል ይኖርብናል። በአዲሱ 2011 ዓመት በኢትዮጵያ የስኬትና የሰላም ዓመት እንዲሆን ከእያንዳንዱ ዜጋ የየራሱን አበርክቶ ይጠበቃል። ለዚህም በፍቅር መደመር በይቅርታ አሮጌውን ዓመት መሻገር ሞራላዊ ግዴታችን ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም