ጽንፈኝነትና አክራሪነትን የሚያራምዱ አካላትን በትብብር መመከት ይገባል- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

124

ሀዋሳ፡ ግንቦት 13/2014 ((ኢዜአ) ) ጽንፈኝነትና አክራሪነትን የሚያራምዱ አካላትን ህዝብና መንግስት በቅንጅት መመከት እንደሚገባ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ለዘመናት የመቻቻልና የሃይማኖት እኩልነት ምሳሌ በሆነችው ኢትዮጵያ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን ለማራመድ በሚሞክሩ ሃይሎች ላይ መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራውን ማጠናከር እንዳለበት  ምሁራኑ አስገንዝበዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና የማህበራዊ ሳይንስና ሥነ- ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳኜ ሽብሩ ለኢዜአ እንዳሉት አክራሪነትና ጽንፈኝነት መነሻቸው የተለያየ ቢሆንም ውጤታቸው አስከፊ ነው።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሃይማኖት፣ በፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች ጽንፍ ይዘው የሚነሱ ቡድኖች የተሻሉ አማራጮች ስለሌላቸው የቀውስ አዙሪት ውስጥ መውደቃቸውን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡ ያልተመቻቸው ቡድኖች የብሔርና የፖለቲካ ልዩነት በመፍጠር የህዝብና የሀገር ሰላምን እያደፈረሱ መሆኑንም ዶክተር ዳኜ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በተለያየ መንገድ የተሞከረው ሀገር የመበታተን ተልዕኮ ባለመሳካቱም በአሁኑ ወቅት ስልቱን ቀይሮ መምጣቱን አንስተዋል።

የመቻቻልና የሃይማኖት እኩልነት ምሳሌ በሆነቸው ኢትዮጵያ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን ለማራመድ በሚሞክሩ ሃይሎች ላይ መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራውን ማጠናከር እንዳለበትም ዶክተር ዳኜ ተናግረዋል።

መንግስት በህዝብና በሀገር ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚወስደው ህግን የማስከበር እርምጃ መጠናከር እንዳለበት አመልክተው፤ "በተለይ በመነጋገርና በመወያየት የሚፈቱ ጉዳዮችን በሀይል ለማስፈጸም መንቀሳቀስ ሀገርን ቀውስ ውስጥ ያስገባል" ብለዋል።

በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ሀገርን ለመበታተን የተነሱ አካላትን ህዝቡ ለይቶ እንዲያውቃቸው በመንግስት በኩል የማስገንዘብ ሥራ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር ዳኜ ገለጻ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ በሀገር አንድነትና አብሮነት ላይ የተሰራው ሥራ ዝቅተኛ መሆን አሁን ላይ እንደ ሀገር ለገጠመው ችግር አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የተበላሹ ጉዳዮችን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ የምክክር ኮሚሽኑ ጅማሮ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርት የሆኑት ወይዘሮ ማህሌት አሸናፊ በበኩላቸው፣ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ አክራሪነትና ጽንፈኝነት በሀገሪቱ እየተስተዋለ መምጣቱን ገልጸዋል።

"የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዓላማን መፈጸም የሚፈልጉ ቡድኖች ወጣቶችን በተለያየ ጥቅማጥቅም በመደለል ወደጥፋት ተግባር ሊያስገቡ ይችላሉ" ሲሉም አክለዋል።

ዜጎች በዚህ የጥፋት ተግባር እንዳይሰማሩ መንግስት ከማስተማር ባለፈ የህግ የበላይነት እንዲከበር መስራት እንዳለበት  አስገንዝበዋል።

አክራሪነትና ጽንፈኝነት ውጤቱ አስከፊ መሆኑን በማስተማር በኩል መንግስት፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት በቅንጅት  መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

 "ወላጆችም በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ የመገንባት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።

"ወጣቶች ሀገርን ለማፍረስ የተደራጁ ጽንፈኛ ሃይሎች መጠቀሚያ ላለመሆን ቆም ብለው ማሰብ፣ ምክንያታዊ መሆንና ኢትዮጵያዊ የአብሮነት እሴትን ማስቀደም ይኖርባቸዋል" ሲሉም መክረዋል።

በሌሎች ሀገራት ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ ያለው በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እና በብሔር ጽንፍ የመያዝና የማክረር አዝማሚያ ለዘመናት ለአብሮነት ምሳሌ ለሆነችው ኢትዮጵያ ጠቃሚ እንዳልሆነም ምሁራኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም