በጋምቤላ ክልል 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር ተወስዶባቸው ወደ ስራ ያልገቡ 92 የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት ለማስገባት እየተሰራ ነው

162

ጋምቤላ፤ ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር ተወስዶባቸው ወደ ስራ ያልገቡ 92 የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።


የባንኩ የስራ ኃላፊዎች ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በእርሻ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።


የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዘዳንት ዶክተር ዩሃንስ አያሌው በውይይት ላይ እንዳሉት በክልሉ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ከሰጣቸው 154 የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል በስራ ላይ የሚገኙት 62 ብቻ ናቸው።


ቀሪዎቹ 92 ፕሮጀክቶች ባለቤቶቹ ልማቱን አቋርጠው መጥፋታቸውን ገልጸዋል።


በዚህም ምክንያት አሁን ላይ በክልሉ ፋይናንስ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ወለዱን ጨምሮ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱንና መሬቶቹም ከልማት ተስተጓጉለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።


በመሆኑም ባንኩ የእርሻ ኢንቨስትመንቶችን በሃራጅ ሽያጭ ለባለሃብቶች በማስተላለፍ ወደ ልማት እንዲገቡ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


ባንኩ ፕሮጀከቶችን ወደ ልማት ለማስገባት በሚያደረገው ጥረት የክልሉ መንግስትና በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ድጋፈና ትብብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል ፕሬዘዳንቱ።


የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ቀደም ሲል በነበሩ ብልሹ አሰራሮች አልሚ ያልሆኑ ባለሃብቶች መሬቱን ለባንክ በማስያዝ የሀገርና ህዝብን ሀብት ዘርፈው መጥፋታቸውን ገልጸዋል።


በዚህም ምክንያት መሬቶቹ ከልማት በመስተጓጎላቻው ህዝቡና የክልሉ መንግስት የሚፈልገውን ልማት ሳያገኝ መቆየቱን ተናግረዋል።


በመሆኑም የእርሻ ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት ለማስገባት በባንኩ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም