ለከፍተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የተደራጀ ቡድን ሊቋቋም ነው

79

ግንቦት 13/2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የተደራጀ ቡድን ሊቋቋም መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

የሚቋቋመው ግብረ ሃይል ከህክምና፣ ፎረንሲክ፣ መረጃና ሌሎች ተቋማት የሚውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ቡድኑን መመስረት የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል።

በኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋን ጨምሮ በሚከሰቱ ሌሎች ከባድ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጎጂዎችን የሚለይ “ዲዛስተር ቪክትም አይደንቲፊካሽን ቲም” እስካሁን አልተቋቋመም።

በዚህም ምክንያት ለአደጋ ፈጥኖ ያለመድረስ፣ ተቀናጅቶ አለመስራት፣ የዘረመል ምርመራ አለማድረግ እና ሌሎችም ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ አደጋዎች ሲገጥሙ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ በአሰራር የተደገፈ ቡድን ማቋቋም ማስፈለጉን በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎሪንሲክ ምርመራ ምክትል ዋና ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ ገልጸዋል።

የሚቋቋመው ቡድን የህክምና፣ የፎረንሲክ፣ የመረጃና ሌሎችም ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የብሔራዊ ኢንተርፖል ሃላፊ ኮማንደር ጸጋየ ሃይሌ፤ ቡድኑ ከተለያዩ አገሮች ልምድ ተወስዶ የሚቋቋም በመሆኑ በአደጋ ወቅት ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።

የቡድኑ መቋቋም በሳይንሳዊ መንገድ የሰዎችን ማንነት መርምሮ ለመለየትና የአደጋን መንስኤ ለማጣራት ለሚደረገው ምርመራም አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

ለዚህም ፌደራል ፖሊስ የዘረ-መል ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል የባለሙያዎችና ላብራቶሪ ዝግጅት ማድረጉ ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር የድንገተኛ ህክምና ቡድን አስተባባሪ ዶክተር ናሆም ታደለ፤ አደጋዎች ሲከሰቱ የሰዎችን ማንነት መለየት የሚያስችል የዘረ መል ምርመራ ለማድረግና ቡድኑን ለማቋቋም የተደረገው ዝግጅት  ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑን ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ትላንት በተጀመረው አውደ ጥናት የወንጀል ምርመራ፣ ጤና፣ መረጃና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ለቡድኑ ምስረታ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ጨምሮ ቀደም ሲል በተከሰቱ አደጋዎች ላይ የነበሩ ክፍተቶች ተለይተው በአውደ ጥናቱ ተዳሰዋል።