የአምራች ዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ለኢትዮጵያ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው

137

ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአምራች ዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ለኢትዮጵያ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “ስለ ኢትዮዽያ፤ ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል ሃሳብ ያዘጋጀው የፎቶግራፍ ኢግዝቢሽንና የፓናል ውይይት ዛሬ በድሬዳዋ ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለው ድርሻ 6 ነጥብ 8 በመቶ እንደሆነና በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።

ይህን ማሳካት የሚቻለው በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚያነሱትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም ፖሊሲዎችና አሰራሮች ቀርጾ በአግባቡ መተግበር ሲቻል መሆኑን አመልክተዋል።

ይሄን ማድረግ ለኢትዮጵያ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግስትና ባለሃብቱ በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ “ኢትዮጵያ ታምርት” አገራዊ ንቅናቄ ከአምራቹ ዘርፍ በተጨማሪ በሁሉም ዘርፍ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጅምር ለውጦች እየተስተዋሉ ናቸው ብለዋል።

መንግስት ለአምራቹ ዘርፍ ተዋናዮች የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልና የግሉ ዘርፍም በምጣኔ ሃብቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ እምቅ ሃብቶች ባሏት ድሬዳዋ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከሁለት ሳምንት በፊት “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አምራች ኢንዱስትሪዎች በግብአት፣ በመሰረተ-ልማት፣ በፋይናንስና ሌሎች ችግሮች ከማምረት አቅማቸው በአማካኝ 50 በመቶ በዝቅተኛ ደረጃ ደግሞ እስከ 10 በመቶ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል ዘላቂነት ያለው እቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በጥሬ እቃ፣ በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማትና ሌሎች ችግሮች ሥራ አቁመው የነበሩ 446 አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመለየት 118 የሚሆኑትን ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ሚኒስትሩ መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ