ለፈንቲ-ረሱ ዞን ነዋሪዎች መሠረታዊ የመንግስት አገልግሎት ሊሟላ እንደሚገባዉ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ

53

ሰመራ፤ ግንቦት 13/2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ተፈናቅለዉ ወደ አካባቢያቸዉ ለተመለሱ የፈንቲ-ረሱ ዞን ነዋሪዎች መሠረታዊ የመንግስት አገልግሎት ሊሟላ እንደሚገባ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።


ተቋሙ በወረራው ምክንያት  ተፈናቅለው  ወደ የአካባቢያቸው በተመለሱባቸው አካባቢዎች ያለውን መንግስታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ አህመድ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአፋር ክልል አካባቢዎች ሰብዓዊ፣ስነ-ልቦናዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።
 
ወረራው ቡድን በየአካባቢው ያስከተለውን ጉዳትና በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለው የመልሶ ግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ከተቋሙ የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል።

 በአውሲ-ረሱና ፈንቲ ረሱ ዞን ስር በሚገኙ በተለያዩ ወረዳዎች ጥናት መደረጉን ጠቁመው ጭፍራ፣ አደአር፣ እዋ፣ አውራ ጉሊናና ወረዳዎችን በአብነት አንስተዋል።

 ወደ የአካባቢው ለተመለሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለመመለስ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

መብራት፣ ስልክ፣ ባንክ፣ትራንስፖርትና መሰል  መሰረታዊ የመንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለእነዚህ አካባቢዎች መንግስት እንደ ጉዳዩ አሳሳቢነት የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ግዜ እቅድ በመያዝ  የመልሶ ግንባታ ስራዎችን  ሊያከናውን ይገባል ብለዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምስራቅ-ምስራቅ ሪጂን ኦፕሬሺናል ማናጀር አቶ አብዱ መሀመድ በበኩላቸው  ጭፍራና ካሳጊታን ጨምሮ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ጉዳት የደረሰባቸው አብዛኛው የፈንቲረሱ ዞን ወረዳዎች  በመሰረተ ልማቱ ላይ ጥገና ተደርጎ ከጥር ወር 2014 ዓ. ም ጀምሮ የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጅ በዞኑ ያሎና ቴሩ ወረዳዎች በአካባቢው የጸጥታ ስጋት በመኖሩ ምክንያት ጥገና ማድረግ ባለመቻሉ  ህብረተሰቡን የአገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ ወሯቸው በነበሩ የተለያዩ የአውሲ-ረሱ፣ ፈንቲ-ረሱና ኸሪ-ረሱ ዞን አካባቢዎች ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ ውድመቶች ማስከተሉን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አፋር ሪጂን ሃላፊ ተወካይ  አቶ መሀመድ አብዱ ናቸው።

ተቋሙ  በወሰደው ፈጣን የጥገና ስራ ተላላክ፣ ደዌና ካሳጊታ አካባቢዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የጭፍራና  እዋና አውራ የመስመር ጥገና ስራቸው መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ የጉሊና ወረዳ  መስመር ጥገናም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን  ተናግረዋል።


የወልድያ  የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ሙሉ በሙሉ   በአሸባሪው ህወሓት በመዘረፉ ምክንያት  የሃይል አቅርቦቱ መቋረጡን ያስታወሱት ደግሞ  የጣቢያው ሃላፊ አቶ ደምስ ሳህለማሪያም ናቸው።

 ከጣቢያው ሃይል ያገኙ የነበሩ  የአፋር ወረዳዎችን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ  ግንባታ የሲቪል ስራው ማለቁን አስታውቀዋል።

 የብረታ-ብረት መገጣጠምና ኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎችም መጀመራቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይ ዓመት የግንባታ ስራው ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የአካባቢዎቹ የሃይል ጥያቄ መልስ ያገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ አሊ በበኩላቸው በዲስትሪክቱ ስር ከሚገኙ ቅርንጫፍ ባንኮች መካከል የጭፍራ ንግድ ባንክ ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ይሁንና በጉሊና ወረዳ የሚገኘው የከልዋን ቅርንጫፍ ባንክ በጸጥታ ችግር ምክንያት ስራ አለመጀመሩን ጠቁመዋል።

የባንኩ ደንበኞች ቆቦና ጭፍራን ጨምሮ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰቡ ክፍሎች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።