የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ልማትን መደገፍ የሚችሉ መሆን አለባቸው

188

አዳማ፣ ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የምርምርና የፈጠራ ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና ልማትን መደገፍ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን አስገነዘቡ።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የተመረጡ ከ210 በላይ የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት 9ኛው ክልል አቀፍ አውደርዕይ ዛሬ በአዳማ በተከፈተበት ወቅት አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት፤ ልማትና ዕድገትን ወደ ፊት ለማራመድ ማህበራዊና ኢኮኖሚ መስኮችን የሚደግፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጋሉ።

በመሆኑም የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበው፤ ተቋማቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የጎላ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

 በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ አገልግሎት፣ ግንባታና ሌሎች ዘርፎች ላይ ተቋማቱ በስፋት የፈጠራና የቴክኖሎጂ ምርምር ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

የክልሉ የስራ ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እድሪስ በበኩላቸው ክህሎትና የፈጠራ ዕውቀትን በማገናኘት ልማቱን በሁሉም ዘርፍ ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት ተቋማቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ የቴክኖሎጂ እገዛ እንዲኖራቸው እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በክህሎ፣ ዕውቀትና በተግባር የበቃ የፈጠራ የሰው ሃይል በመገንባት ማኑፋክቸሪንግና የኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ በቀጣይነት የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

860 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ደረጃዎች መዘጋጀታቸውን የገለፁት ሃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት 160 የሚሆኑ ደረጃዎችን ወደ ስልጠና አስገብተናል ብለዋል።

በክልሉ 21 ዞኖችና 19 የከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 228 ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የተመረጡ 210 አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችና ቴክኖሎጂችን ይዘው ለሶስት ቀን በሚቆየው በዚህ አውደርዕይ ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም