በዞኑ ከ100 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቄያቸው ተመለሱ

158

ግንቦት 13/2014 ነቀምቴ /ኢዜአ/ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ 112 ሺህ ወገኖች ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ ፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ወጋሪ ነገራ ለኢዜአ እንደገለጹት ወደ ቄያቸው የተመለሱ ወገኖች በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎችና በከተሞች ተጠልለው የቆዩ ናቸው።

በዞኑ የፀጥታ ችግር አጋጥሞ በነበረባቸው አካባቢዎች መንግሥት፣ የፀጥታ ኃይሉና፣ ሕዝብ በቅንጅት በሰሩት ሥራ አንፃራዊ ሠላም በመስፈኑ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ሆነው ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት የመልሶ ማቋቋም ሥራ እያካሄዱ መሆኑን አመልክተዋል።

የምግብ ችግር እንዳይገጥም መንግሥትና በዞኑ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለሕፃናት ጭምር አልሚ ምግቦችን በየወቅቱ  ለማዳረስ የዞኑ የአደጋ ሥጋት ኮሚቴ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይ ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ርቀው ለሚገኙ ሐሮ ሊሙ፣ ሊሙ፣ ጊዳ አያና እና ኪረሙ  ወረዳዎች   የእርዳታ እህል የማዳረሱ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የእርሻ ወቅት ከማለፉ በፊት መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቸ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ለቺሣ  እንዳሉት ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሰሩ ነው።

በዚህም ለሲቡ ስሬ፣ ለሐሮ ሊሙ፣ ለኪረሙ እና ለዋዩ ቱቃ ወረዳዎች ለመጠለያ የሚያገለግሉ ሸራዎችን እንዲደርሳቸው  መደረጉን አስታውቀዋል።

 ኃላፊው  እንዳሉት እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የሚበቃ  የቀለብ እህል በዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር መጋዘን ደርሷል።

በዋና መንገድ ላይ ለሚገኙ ዲጋ፣ ሳሲጋ፣ ጉቶ ጊዳ፣ ሌቃ ዱለቻ፣ ዋዩ ቱቃ፣ ሲቡ ስሬና ጎቡ ሰዮ ወረዳዎች  እርዳታን በቀላሉ ማድረስ የሚቻልበት አስተማማኝ ምቹ ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።

በጉቶ ጊዳና ሳሲጋ ወረዳዎች ለሚገኙ ለ2 ሺህ አባወራ ተፈናቃዮች ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶ እንዲሰጣቸው ከወረዳዎቹ አመራሮች ጋር  ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርና የልማት ተነሺዎች መጋዘን የሚገኙ እንደ ማረሻ፣ ሳፔታ እና ገሶ የመሳሰሉት   የተለያዩ የእርሻ መሣሪዎች የተሰጣቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ የሆሮ አለልቱ ቀበሌ ነዋሪው ተፈናቃይ አርሰ አደር ክብሩ ወዳጆ በሰጡት አስተያየት አሁን ወደ ቄያቸው ተመልሰው ዳስ ሰርተው መኖር መጀመራቸው ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

ተረጋግተው የእርሻ ስራቸውን ማካሄድ እንዲችሉ እስኪቋቋሙ ድረስ የምርት ግብዓቶችና ቀለብ በመስጠት መንግሥት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ወጣት ቢልሱማ ክብሩ በሰጠው አስተያየት  በወረዳው የሆሮ ሀለልቱ የገጠር ከተማ የመሰረተ ልማት ውድመት በመድረሱ  የመብራት፣ የንጹህ የመጠጥ  ውኃ  አገልግሎት እና የእህል ወፍጮ አገልግሎቶች እንደሌሉ ተናግሯል።

ህብረተሰቡ ከመንግሥት የተሰጠውን የእርዳታ እህል ለማስፈጨት የ35 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተጓዘ በመሆኑ ይህን በተቻለ መጠን ወደ ቀድሞው ለመመለስ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብሏል።

አርሶ አደር ደሱ ሞላ በበኩላቸው ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎ  ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን ገልጸው አሁን ወደ ቀድሞ ቄያቸው ተመልሰው እርሻ ቢጀምሩም የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እጥረት እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

ከብት ሽጠው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ገዝተው ዘር መዝራት መጀመራቸውን ተናግረው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው  ጠይቀዋል፡፡

በጉቶ ጊዳ ወረዳ የሆሮ ሀለልቱ የገጠር ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ መልካሙ ጊዲሣ በበኩላቸው ሕዝቡ ወደ ቄየው ቢመለስም በከፍተኛ ማህበራዊ ችግሮች ያሉ በመሆኑ የመንግሥት ልዩ ትኩረትና የባለድርሻ አከላት ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም