ኢትዮጵያ ከ25 ዓመት በታች የአፍሪካ የሴቶች ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ታስተናግዳለች

92

አዳማ፤ ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከ25 ዓመት በታች የአፍሪካ የሴቶች ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር እንደምታዘጋጅ ተገለጸ።

መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ለውድድሩ ዝግጅት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ሶስተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን አቶ አባይነህ ጉጆ የአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ከ25 ዓመት በታች የአፍሪካ የሴቶች ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር እንድታስተናግድ መምረጡን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጥር ወር 2014 ዓ.ም 11ኛው የአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድርን በብቃት በማስተናገዷ ውድድሩን እንድስታናግድ ለመመረጧ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ውድድሩ የሚካሄድበት ቀን ያልተቆረጠለት ቢሆንም እ.አ.አ በ2022 እንደሚካሄድ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የዝግጅት ስራዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል።

መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ለውድድሩ ዝግጅት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ አቶ አባይነህ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ ወይዘሮ ፈይሰል አማከለ በበኩላቸው ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞች በሁሉም የስፖርት መስክ ያላቸውን ተሳትፎና የስፖርቱን ውጤታማነት ለማሳደግ ከአሶሴሽኑ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን በሶስተኛ ጠቅላላ ጉባኤው የ2015 ዓ.ም እቅድ ላይ በመወያየት ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሶስት ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ስፖርቱን የማሳደግና የማስፋፋት ኃላፊነት ተሰጥቶት በመስራት ላይ ይገኛል።

11ኛው የአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች በራስ ኃይሉ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ከጥር 15 እስከ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

በወንዶች ግብጽ እንዲሁም በሴቶች አልጀሪያ የውድድሩ አሸናፊ ሲሆኑ፤ኢትዮጵያ በሴቶች ሶስተኛ በወንዶች አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️