የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በውጤታማነታቸው ስምና ዝና እያተረፉ ያሉ አትሌቶችን እያፈራ ነው

74

ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አገር ወክለው ውጤት በማምጣት ስምና ዝና እያተረፉ ያሉ አትሌቶችን እያፈራ ነው።

የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በ2004 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ዋና ዓላማውም ተሰጥኦ ያላቸው አትሌቶች እድል አግኝተው ለክለቦችና ብሄራዊ ቡድን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

በማዕከሉ የሚሰጡ ስልጠናዎች በአትሌቲክስ ስፖርት ሩጫን ጨምሮ የሜዳ ላይ አትሌቲክስ ተግባራትን ያካተተ ነው።

በእነዚህ ዘርፎች እስካሁን 223 ስፖርተኞችን አሰልጠኖ 197 ለክለብ በማስመረጥ በውጤታማ ጎዙ መቀጠሉን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሃይሉ ለማ ገልጸዋል።

በማዕከሉ እስካሁን ከሰለጠኑት ወጣቶች መካከል ከ80 በመቶው በላይ ወደ ክለብ መሸጋገራቸውን አስታውሰው ዓለም አቀፍ ስምና ዝና ያተረፉ እንዳሉም ገልጸዋል።

ከሚጠቀሱት አትሌቶች መካከል ነጻነት ጉደታ እና ታምሩ ከፍያለው ከማዕከሉ ከወጡት ስፖርተኞች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አትሌት ነጻነት ጉደታ በረጅም ርቀት በተለይም በግማሽ ማራቶንና አገር አቋራጭ ውድድር ስኬታማ ከሆኑ አትሌቶች መካከል የምትጠቀስ ናት።

አትሌት ታምሩ ከፍያለው በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ በፓራ ኦሊምፒክ መሳተፍ የቻለ አትሌት መሆኑንም አስታውሰዋል።

የበርካታ አትሌቶች ማፍሪያ የሆነው ማዕከሉ ለሁለት ዓመታት ይሰጥ የነበረውን የስልጠና ጊዜ በማሻሻል ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወደ አራት ዓመት ከፋ አድርጓል።

በማዕከሉ አሁን በስልጠና ላይ የሚገኙት እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ 20 ወንድ እና 20 ሴት ስፖርተኞች ሙሉ ወጪያቸው በክልሉ መንግስት ተሸፍኖ በስልጠና ላይ ይገኛሉ።

ከክልሉ መንግስት ውጪ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የትጥቅ ድጋፍ በማድረግ እያገዘ መሆኑ ታውቋል።