ሀዋሳን ጽዱ፣ ውብ፣ ለኑሮ ምቹና የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፤ ግንቦት 13/2014 (ኢዜአ ) ሀዋሳ ከተማን ጽዱ፣ ውብና ለኑሮ ምቹና የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳዳደሩ ከንቲባ አስታወቀ።

''ውብና ምቹ ከተማ እንፍጠር'' በሚል መሪ ሀሳብ በከተማዋ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።

የከተማዋ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንዳሉት የከተማው አስተዳደር ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

ከተማዋ ጽዱና አረንጓዴ እንዲሁም በጎብኚዎች ዘንድ ተመራጭ እንድትሆን ለማድረግ በሁሉም ነዋሪዎችና የንግድ ተቋማት ከጽዳት ሥራ በተጨማሪ ለውበት የሚሆኑ ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘመቻው በየሳምንቱ እንደሚከናወንም ከንቲባው ጠቅሰው፤ ክረምት መግባቱን ተከትሎ በየአካባቢው የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችን ጠረጋ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በማጽዳት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ በሚያደርጉ ተግባራት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

የከተማውዋ ምክትል ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ በትሬ በበኩላቸው ሀዋሳን ውብ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሃዋሳን በጽዱ፣ ውብና  ለኑሮ ምቹና የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል በሀዋሳ ሀይቅ ዙሪያ የሚገኙ ስፍራዎችን ለማስዋብ የውበት ዛፎችና እጽዋትን ማልማት ይገኙባቸዋል።

እንዲሁም በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ዳር አረንጓዴ ስፍራዎችን ማልማት እንደሚገኝበት ጠቁመዋል።

በጽዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ እንዳሉት ሀዋሳ ንጽህናዋ የተጠበቀና ውብ በመሆኗ በጎብኚዎች ተመራጭ ናት።

ከብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ በኋላ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አመራሩን የሚገመግም ቡድን በመምራት በከተማዋ እንደተገኙም አስረድተዋል።

ዶክተር በከር አክለውም የከተማ አስተዳደሩ የጽዳት ዘመቻ እንደሚያካሂድ ሲሰሙ በዘመቻው ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀዋሳን ውበት ለማስጠበቅና ጽዳቷን ለመጠበቅ እንቅስቃሴው መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በዚህም የከተማዋን ንጽህና በመጠበቅ ረገድ ህዝብና አመራሩ ተቀራርበው በጋራ የሚያከናወኑትን ስራ መመልከታቸውንም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም