የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ አሸናፊነት የሚያንፀባርቅ ነው የተባለ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት በድሬደዋ ተከፈተ

143

ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ስለ ኢትዮጵያ " በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያን አሸናፊነት እና ከፍታን የሚያመላክት የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ዛሬ በድሬደዋ ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከጅግጅጋ ቀጥል ድሬደዋ ላይ ዛሬ ያዘጋጀውን ይህን የፎቶ አውደ ርዕይ የከፈቱት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።

የፎቶ አወደ ርዕዩ ከ1960 ዎቹ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ተስፋ እስከጣለችበት የሪፎርም ለውጥ ማግስት ያለውን ሁለንተናዊ ገፅታ እና ለህልውናዋ መረጋገጥ ያካሄደችውን የህልውና ዘመቻ ቁልጭ አድርጎ ተንፀባርቆበታል።

"ኢትዮጵያ አያሸነፈች ትሻገራለች" በሚል መሪ ሀሳብ ከተዘጋጀው የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ በተጨማሪ "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሃሳብ በመላው አገሪቱ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ያመጣቸው ውጤቶች፤በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎች፣ ዘርፉ በሚቀጥሉት 10 አመታት በአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ሂደት የድርሻውን ሚና እንዲያበረክት ያሉ ምችችቶች ላይ ያጠነጠኑ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

ውይይቱን የሚመሩት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ፣የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ፣የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ ናቸው።

በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የባለሃብቶች ወኪል የኢንዱስትሪ ልማትን አስመልከተው ፅሁፍ ያቀርባሉ።

ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው በዚህ የፎቶግራፍ አውደ ርእይ ላይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማንን ጨምሮ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች አመራሮች ፣ባለሀብቶች ፣የአገር ሽማግሌዎች ፣አባገዳዎች፣የአገር ሽማግሌዎች ተሳታፊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም