በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደረገ

84

ሰቆጣ፤ ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ )፡ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ዱቄትና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና በአዲስ አበባ የአማራ ወጣቶች ማህበር አማካኝነት የተደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተወካይ አቶ ተራመድ ይልማ በድጋፍ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት ድጋፉን በደቡብ አፍሪካ ኡምታታ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተሰባሰበ ነው።

ትውልደ ኢትዮጵያኑ ባሰባሰቡት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር 322 ኩንታል የምግብ ዱቄት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ የአማራ ወጣቶች ማህበር የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ወጣት እዩኤል ጌትነት በበኩሉ ማህበሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ አባላቱንና ነዋሪዎችን በማስተባበር 1 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸውን ቁሳቁሶች  ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ አልባሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስና የንፅህና መጠበቂያዎችን ያካተተ መሆኑን አመልክቷል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ ስቡህ ገበያው በበኩላቸው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ድጋፍ የወገን አለኝታ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

የተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን የምግብና አልባሳት ችግርን የሚያቃልል መሆኑን ተናግረዋል ።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ትወልደ ኢትዮጵያዊያንና በአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ለተፈናቀሉ ወገኖች ለተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ88 ሺህ በላይ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ ወለህ እና ፅፅቃ መጠለያ ጣብያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ተመላክቷል።