የአዲስ አበባ ብልፅግና ወጣቶች ሊግ ያሰባሰበውን ከ3 ሺህ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተመጻሕፍት አበረከተ

146

ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ብልፅግና ወጣቶች ሊግ አባላቱና ወጣቶችን በማስተባበር ያሰባሰበውን ከ3ሺህ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት "ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ ለአንድ ወር የሚቆየውን የመጻህፍት ማሰባሰብ ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ብልፅግና ወጣቶች ሊግ አባላቱንና ወጣቶችን በማስተባበር ያሰባሰበውን ከ3 ሺህ በላይ መጻሕፍ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በዛሬው ዕለት አበርክቷል።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት በቀለ ታጀበ ቢሁ ጊዜ እንደገለጹት፤  የበለጸገች አገር ለመፍጠር ሚዛናዊና አንባቢ ወጣት መፍጠር ያስፈልጋል።

ትልቅ ራዕይና ዓላማ አንግቦ የተቋቋመውን አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ለወጣቶች የተመቸ ለማድረግ ጠንክረን መሥራት ይጠበቅብናልም ብሏል።

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የበላይ ጠባቂ ኢንጂነር ውባየሁ ዓለማየሁ በበኩላቸው የተበረከቱት መጻህፍት የትውልድን አእምሮ ለማበልፀግና ቀጣይ ሕይወቱን ለማስመር የሚረዱ ናቸው ብለዋል።      

መጻሕፍትን ወደ ሕያው ቤታቸው ቤተ-መጻሕፍት ማምጣት ብሎም ሰዎች እንዲያነቡ ማበረታታት የሁሉም ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው የሚያጠፋ ሳይሆን የሚያርም ትውልድ ለመፍጠር ንባብ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።

አብርሆት ቤተ መጻህፍት ከአራት ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት እንደሚያስፈልገው ገልጸው ይህን ለማሟላት ተጋግዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም