በመስኖ ፕሮጀክት ዲዛይንና የአዋጭነት ጥናት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ መሬት ነክ መረጃዎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል

110

ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) በመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ እስከ አምስት እጥፍ ለሚደርስ ወጪ እየዳረጉ ያሉ የዲዛይንና የአዋጭነት ጥናት ችግሮችን ለመቅረፍ መሬት ነክ መረጃዎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ።

በመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ የዲዛይንና የአዋጭነት ጥናት ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ የምክክር አውደ ጥናት ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ ኢንጂነር ሳሙኤል ሁሴን መንግሥት ለመስኖ ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም 18 ቢሊዮን ብር በመመደብ የትላልቅና የአነስተኛ ግድቦች ግንባታ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ዘርፉ አሁንም ችግሮች እንዳሉበት ያነሱት ኢንጂነር ሳሙኤል፤ በአነስተኛና ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነት ጥናት፣ የዲዛይንና የግንባታ መጓተት ፈተና መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

ለዲዛይንና የአዋጭነት ጥናት ችግሮች መነሻ የሚሆኑት ደግሞ የመሬት አቀማመጥ፣ የአካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታ፣ የከርሰ ምድር ይዘትና መሰል በቴክኖሎጂ የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ አለመጠቀም ነው ብለዋል።

በዚህም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ለማጠናቀቅ አለመቻሉን በማንሳት የፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻያል ኢንስቲትዩት የመሬት ምልከታ ተመራማሪው ዶክተር ወርቁ ዘውዴ፤ በመስኖ ፕሮጀክቶች ወቅት ከመሬት ምልከታ የሚገኙ መረጃችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ትክክለኛ የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን መሥራት ይቻላል ይላሉ።

በተለይም ግንባታ ሊካሄድባቸው የታቀዱ ቦታዎችን ዝርዝር ሁኔታ ከተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥና ባህሪ እስከ ማህበረሰብ አሰፋፈር በጥልቀት በማጥናት የፕሮጀክት ዲዛይኖችን ማገዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

መስኖ ፕሮጀክቶቹ ከተገነቡ በኋላም ክትትል ለማድረግ የመሬት ምልክታ መረጃዎች ጠቃሚ መሆናቸውን በማንሳት።

በሚኒስቴሩ የጥናትና ዲዛይን ዳይሬክተር ኢንጂነር እንግዳሰው ዘርሁን፤ የፕሮጀክት ዲዛይን አማካሪዎችና አጥኝዎች ከመሬት ወደ ታች የሚደረግ የአፈር ምርምራ ላይ የአቅም ክፍተት በመኖሩ  ተገቢ የዲዛይንና አካባቢያዊ የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ መቸገራቸውን ገልጸዋል።

የጥናትና ዲዛይን ችግሮች ደግም ለፕሮጀክት ግንባታው መጓተት ዓቢይ ምክንያት መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በቀጣይ ሚኒስቴሩ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ሳይንሳዊ መረጃዎችን በመጠቀም  ፕሮጀክቶችን ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ይሰራል ብለዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶች ከእቅዳቸው እስከ አምስት እጥፍ ወጪ እየጠየቁ መሆኑን ያበራሩት በሚኒስቴሩ የአቅም ግንባታና የመስኖ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ዘበነ ወርቁ፤ ከፍተኛ የጊዜ መጓተት ይስተዋልባቸዋል ነው ያሉት።

በቀጣይም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ በቅንጅት እንሰራለን ነው ያሉት።