የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

175

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል፣ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለ10ኛ ጊዜ ያዘጋጀው አውደ ጥናት በዩኒቨርስቲው እየተካሄደ ይገኛል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሚልኬሳ ጃገማ ለኢዜአ እንዳሉት የጨርቃጨርቅ፣አልባሳት፣የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የኢትዮጵያ እምቅ የገበያ እድል በመሆን ተለይተው ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ለዚህም በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አቅም ያላቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል እንዲያጠናክሩ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ የእውቀት፣የክህሎትና የግብዓት አቅርቦት በመፍታት በምርት ተወዳዳሪ በማድረግ የሃገር ውስጥ ገበያን በመሸፈን ወደ ተለያዩ የውጭ ሃገራት የተሻለ ምርት ማቅረብ እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ ነው።

የሃገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በጥናትና ምርምር እንዲታገዙም ይደረጋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀው፤ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ የሚያደርጉ ችግሮችን በመለየት በቅርበት መፍትሄ እየተሰጠ ይገኛል።

አሁን ላይ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ50 በመቶ እንደማይበልጥ አመልክተው፤የስራ ባህልን በማሻሻል፣የሰለጠነ የሰው ሃይል በመጠቀምና በቴክኖሎጂ በማጠናከር ምርታማነታቸውን እንዲያድግ ይደረጋል።

የሚስተዋሉ እጥረቶችን በመፍታትና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን አቅም በማጠናከር ዘርፉ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት አሁን እያበረከተ ካለው 6 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻውን በቀጣይ 8 ዓመታ 17 ነጥብ 8 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

የኢንዱስትሪዎችን ምርት በጥራትም ሆነ በብዛት በማሳደግ የሃገር ውስጥ ገበያውን ከማስፋት ባሻገር ባለፈው ዓመት 470 ሚሊዮን ዶላር የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የኢትዮጰያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዘርፉ የሚስተዋሉ የእውቀትና የክህሎት ክፍተቶችን በጥናት በመለየት ለማገዝ እያደረገ ያለው ጥረትም የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።

''ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ጠንካራ ስራ እየተሰራ ነው''ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ተስፋየ ናቸው።

በሃገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በተለይም የበቃና የሰለጠነ የሰው ሃያልና የፍትሻ ላቦራቶሪ ክፍተት ሰፊ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህነኑ ለመፍታትም ኢንስቲትዩቱ ተግብር ተኮር ስልጠና በመስጠት የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማፍራት ጎን ለጎን ኢንዱስተሪዎች ያለባቸውን የኬሚካል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት አማራጭ ኬሚካል ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በጨርቃጨርቅ፣ አልባሳትና ቆዳ ውጤቶች በተሻለ ጥራት ተመርተው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት የሚችል የሰው ሃይል በብቃት የማፍራት ስራ እየተከናወነ ነው።

በአሁኑ ወቅት በተለያየ ፕሮግራሞች ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተመረ እንደሚገኝ አመልክትው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪዎችን ችግር በጥናትና ምርምር በመለየት የማገዝ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በአውደ ጥናቱ ከ44 የማያንሱ ጥናታዊ ፅሁፎች እየቀረቡ ሲሆን ከሃገር ውስጥና ከተለያዩ የውጭ ሃገራት የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛል።

እንዲሁም ፋሽን ሾ፣ኤግዚቢሽንና ባዛር የፕሮግራሙ አካል መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም