ቪንትስ የተሰኘው የኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ለሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት ገንብቶ አስረከበ

119

ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ)፡በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እያመረተ የሚገኘው ሺንትስ የተሰኘው የኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ለሠራተኞቹ በፓርኩ ውስጥ መኖሪያ ቤት ሰርቶ አስረከበ።

ኩባንያው ከ5 ሺህ 100 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ከዚህም ውስጥ ለ2 ሺህ 700 ለሚሆኑት ሠራተኞቹ ነው ዛሬ የመኖሪያ ቤቱን ያስተላለፈው።   

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ሰለሞን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የቤት ችግር ሠራተኞች ምርታማ እንዳይሆኑ አንዱ ተግዳሮት ነው።  

ቪንትስ የተሰኘው የኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያም ለሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት መገንባቱ ሠራተኞቹ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ተረጋግተው እንዲሰሩ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን የኩባንያውን ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምር ተናግረዋል። ይህንን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ፓርኮች የማስፋት እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።  

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ ባለሃብቶች የመሥሪያ ቦታ ወስዶ የመኖሪያ ቤት ለመሥራት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የቤት ችግር ለመቅረፍ ፓርኮቹ የሚገኙባቸው ከተሞችም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ለፓርኮቹ የመሬትና የውሃ አቅርቦት በመንግሥት በኩል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሠራተኞቻቸው የመኖሪያ ቤት ስለሚፈልጉ ቤት መሥራት ቢጀምሩ ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌሎች ባለሀብቶች የዚህን ፋብሪካ ምሳሌ በመከተል ቤት በመሥራት ለሠራተኞች መስጠት አለባቸው ሲሉም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በአገሪቱ ከ85 ሺህ በላይ ሠራተኞች በፓርኮች ውስጥ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም ለሠራተኞቻቸው ቤት ገምብቶ መስጠት አለባቸው ብለዋል።

ኩባንያው እየሰራው ላለው የማስፋፊያ ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ እንዲህ አይነት ምሳሌ የሚሆን ሥራ ለሚያከናውኑ ባለሃብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ከኩባንያው ሠራተኞች ኢዛዲን አባጉምቡልና ዮናታን ዳኒኤል በበኩላቸው የመኖሪያ ቤት ችግር እንደነበረባቸው ጠቁመው፤ ባገኙት ዕድል መደሰታቸውንና ይህም በሥራቸውም ላይ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።