በብሔረሰብ አስተዳደሩ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

104

ሰቆጣ፤ ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ)፡ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ295 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ መከላከያ ክትባት ሊሰጥ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱን ከግንቦት 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል።

ክትባቱ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ 295 ሺህ  ወገኖች ተደራሽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ክትባቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ጨምሮ ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አምስት ወረዳዎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ይሰጣል።

ለጤና ባለሙያዎችና አመራሮች የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን ገልጸዋል።

በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የሚሰጥ በመሆኑ  የሚመለከታቸው ወገኖች ክትባቱን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።