በኦሊምፒክ ኮሚቴና በፌደሬሽኖች መካከል መልካም የሥራ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል

147

 አዲስ አበባ  ግንቦት 12/2014 /ኢዜአ/ በኦሊምፒክ ኮሚቴና በፌደሬሽኖች መካከል የሥራ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ቀጀላ መርዳሳ ገለፁ።

ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበበት የቶኪዮ 2020  ኦሎምፒክ  ተሳትፎን በተመለከተ  የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣  አትሌቲክስ ፌደሬሽን፣ ውሃ ስፖርቶች፣  ብስክሌት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይቱ ተካሂዷል።

ቶኪዮ 2020 ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መሳተፍ ከጀመረችበት 1956 ሜልቦርን ጀምሮ ሁለተኛው ከፍተኛ ስፖርተኞች ያሳተፈችበት ነው።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ፌደሬሽኖች በተፈጠረው አለመግባባትና ሌሎች ምክያቶች የሚፈልገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም።

በቀጣይ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ኮሚቴ ና አትሌቲክስ ፌደሬሽንን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ማኅበራትና ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጋራ እንዲሰሩ ያለመ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ችግሮች የነበሩበት ነው ብለዋል።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች በማጎልበትና ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ በሚካሄደው ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት  ማስመዝገብ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ለዚህም ስፖርቱ ጤናማ በሆነ መልኩ መመራትና በትብብር መሰራት አለበት ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በኦሊምፒክ ኮሚቴና በፌደሬሽኖች መካከል መልካም የሥራ ግንኙነትን ለመፍጠር ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች በመግለፅ።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ኦሊምፒክ ኮሚቴ መመሪያንና አሰራርን አክብሮ የሚሰራ ነው።

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ሲያደርጉ የነበሩት ሌሎች አካላት መሆናቸውን ጠቁመው ጉዳዩ ይህንን ያክል የተጋነነ አልነበረም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ሁሉም በተሰጠው ሃላፊነትና ሥልጣን ልክ ብቻ መሥራት አለበት ብላለች።

በቀጣይ ኦሊምፒክ በትብብር በመሥራት ከተቻለ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብላለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር በዛብህ ወልዴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እንደተሞክሮ የሚጠቀስ አሰራርና አደረጃጃት ያለው እንደሆነ አንስተዋል።

በቀጣይም ይህን አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው የስፖርት አንዱ ችግር የግል ፋላጎት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በቀጣይ ስፖርት ያለውን የገንዘብ ዝውውር የሚከታተልና ተጠያቂ የሚያደርግ የፀረ-ሙስና አደረጃጀት ማዋቀር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም