ዩኒቨረሲቲው አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማገባደዱን ገለጸ

84

ሆሳዕና፤ ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) የወራቤ ዩኒቨረስቲ አዲስ ገቢ የተመደቡለትን ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ዩኒቨረሲቲው የመማር ማስተማር ስራዉን ከጀመረበት አንስቶ የዘንድሮው ለአምስተኛ ዙር የሚከናወን የተማሪዎች ቅበላ መሆኑ ተመላክቷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መሀመድ አዎል ዩኒቨርስቲዉ ዘንድሮ የተመደቡለትን ከ3 ሺህ 200 በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በመጪው ግንቦት 15 እና 16 ለሚቀበላቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎችም ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዩንቨርስቲው ከወራቤ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አዲስ የተመደቡ ተማሪዎችንና ወላጆቻቸዉን ጨምሮ ሳይንገላቱ ወደግቢ እንድገቡ ለማስቻል የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎች ማመቻቸቱን ገልጸዋል

ከዚህ ቀደም ወደ ዩኒቨርስቲው አዲስ ይመደቡ ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር  በዘንድሮው አመት ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ይህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ለተማሪዎቹ የሚሆን የመማሪያ፤የማደሪያና መመገቢያ አዳዲስ ህንፃዎችንና አዳራሾችን ጨምሮ ዉሃና መብራት አስፈላጊ ነገሮች ማሟላት ያካተተ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው ያስታወቁት።

በወራቤ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ አብድልሀሚድ አስፋው በበኩሉ አዲስ በተመደቡ ተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጨምሮ ከሁሉም የዩኒቨረቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግሯል።

አዲስ ገቢ ተማሪዎቹ በአካባቢው ከደረሱ በኋላ ያለ ምንም እንግልትና ችግር ወደግቢ እንድደርሱ የሚያግዝ ነባር ተማሪዎችና የከተማ ወጣቶች ያካተተ አደረጃጀት መዋቀሩን ገልጿል

አዲስ ወደ ዩንቨርስቲው የተመደቡ ተማሪዎች ለመጡለት ዓላማ እንዲቆሙ በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል በህብረቱ በኩል የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰራም ገልጿል።

በአካባቢው ተከስቶ ከነበረው ችግር መነሻ በቤተሰብና በተማሪዎች ዘንድ ስጋት እንዳይፈጠር የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ልዩ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በ2010 ዓ.ም ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የወራቤ ዩኒቨረሲቲ አሁን ላይ ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ መርሐ ግብር ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨረሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።