ልጆች በመልካም ስብዕና ታንጸው እንዲያድጉ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት

74

 አዲስ አበባ  ግንቦት 12/2014 /ኢዜአ/ ልጆች በመልካም ስብዕና ታንጸው ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የቅን ኢትዮጵያ ማኅበር አሳሰበ።

የትምህርት ሚኒስቴርና ቅን ኢትዮጵያ ማኅበር ሁለተኛውን ሀገር አቀፍ የተማሪዎች፣ የመምህራንና የወላጆች የመመሰጋገንና የመደናነቅ ቀን አከበሩ።

በእለቱ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የቅን ኢትዮጵያ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ስዩም፤ መልካም ስብዕና የተላበሰ ዜጋ ለማፍራት ወላጆችን ጨምሮ የሁሉም ማኅበረሰብ ሚና ሊታከል ይገባል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ልጆች በመልካም ስብዕና ታንጸው ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያን እሴቶች በማስተማር የመደናነቅ፣ የመከባበር እንዲሁም ሌሎች በጎ ምግባሮችን እዲያዳብሩ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ለዚህ ስኬት ደግሞ በአዲሱ ትውልድ ላይ ቅንነትን የሚያሰርጹ ተግባራትን ማከናወን ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

የቅን ኢትዮጵያ ማኅበር መሥራች ዶክተር ቶሎሳ ጉዲና፤ የቅንነት መጓደል የሚስተዋልባቸው ሰዎች በተተኪው ትውልድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ለልጆች መልካም ስብዕና መላበስ የሁላችንም በጎነትና አርአያነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

በመርሃ ግብሩ የታደሙ መምህራን በበኩላቸው፤ ልጆችን ከማስተማር ባለፈ መልካም ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉ የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

በመሆኑም ተማሪዎች  በቅንነት፣ በመቅረብ እርስ በርስ እንዲመሰጋገኑና እንዲደናነቁ በማድረግ ጥሩ ዜጋ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን ነው ያሉት።