በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከ75 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በአፋር ክልል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል

78

ሰመራ፣ ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ከ75 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በአፋር ክልል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በጦርነት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማነቃቃትን አላማ ያደረገ የሁለት ቀናት ስልጠና ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀምሯል።

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር የአሸባሪው ሕወሃት ወረራና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በክልሉ ቱሪዝም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማነቃቃት አፋር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የከፈለውን መስዋዕትነት በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረውን በጎ ተጽእኖ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘርፉን የማስተዋወቅ ስራዎች ሲከናወኑ መቆያታቸውን ተናግረዋል።

ክልሉ የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ በሆቴል አገልግሎት እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን የማመቻቸት እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመለየት፣ ማልማትና የማስተዋወቅ ስራዎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ነው አቶ አህመድ ያስረዱት።

በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የአፋር ክልል የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳለው የጠቀሱት የቱሪዝም ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በማልማትና ጥቅም ላይ በማዋል ለአገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለያየ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የውጭ ቱሪስት ፍሰት ከማሳደግ ጎን ለጎን የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ቁጥር ለማሻሻል መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ  እንደ ከኢድ እስከ ኢድና መሰል የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የሚያነቃቁ መርሃ ግብሮች  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ በጋሻው ቅጣው የስራ እድል ለመፍጠር እምቅ አቅም ባለው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።