ወታደሩ በእውቀትና በብልሃት ተልዕኮውን እንዲፈጽም ዋር ኮሌጅ በተደራጀ ሁኔታ እየተዋቀረ ነው

189

ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) ወታደሩ በእውቀትና በብልሃት ተልዕኮውን እንዲፈጽም ዋር ኮሌጅን በተደራጀ ሁኔታ የማዋቀር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ ታደሰ ተናገሩ።

ዋና አዛዡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ዘመናዊ የውጊያ ስልትንና ተግባቦትን አሰናስሎ ለማካሄድ ሰራዊቱ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሊደገፍ ይገባል።

ወታደር ከሃይማኖት ከብሔርና ከፖለቲካ አስተሳሰብ በጸዳ መልኩ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማድረግ መሪው በሃላፊነትና በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቀበታል ብለዋል።

ለተልዕኮውም ፍጹም ታማኝ በመሆን በህዝቡና በአገሩ የተጣለበትን አደራ በብቃት መፈጸም ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።

''ወታደር በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሥራን እንጂ ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር የሥርዓቱ አራማጅ መሆን የለበትም'' ያሉት ብርጋዴር ጄነራሉ ለዚህም ሰራዊቱን በሙያዊ ሥልጠናዎች ማብቃት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለዚህም ዋር ኮሌጅን በተደራጀ መልኩ በማዋቀር ወታደሩ በእውቀትና በብልሃት ተልዕኮውን እንዲፈጽም መደገፍና ማብቃት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።   

በዋር ኮሌጅ የሚሰጡ የትምህርት አይነቶች ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ይህም በኮሌጁ የሚሰጡ ትምህርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር ወደ ተግባር ሲገባ ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ ታልሞ መሆኑን በመጠቆም።

በኮሌጁ ወታደሩ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሴክተሮች ያሉ የጸጥታ አካላት እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችም ጭምር የተለያዩ የትምህርት አይነቶችንና ሥልጠናዎችን የሚያገኙበት እድል ተመቻችቷል ብለዋል።    

በኮሌጁ በቂ መምህራን እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሟሉ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተለያዩ የመማሪያ፣ የሥልጠናና ሲምፖዚዬም የሚካሄድባቸው ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በትብብር ከሚሰሩ ተቋማት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከምርምር ማዕከላት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥምምነቶች መደረጋቸውን ገልጸው ኮሌጁ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

በዋናነት ኮሌጁ የትኛውንም አገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም አስቻይ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ለዚህም ዝግጁ መሆኑን የኮሌጁ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም