አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እንዲያረጋገጥ ተጠየቀ

ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአካል ጉዳተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ እንዲያረጋገጥ የአካል ጉዳተኛ አደረጃጀቶች ጠየቁ።

ምክክር ኮሚሽኑ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች አደረጃጅቶች ጋር ስለኮሚሽኑ ሥራዎች ውይይትና ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።

በውይይቱም የአገራዊ ኮሚሽን ኮሚሽኑ በቀጣይ ሥራዎቹ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ና በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ዕውቅ ቢያገኙም በርካታ ያልተመለሱ አጀንዳዎች እንዳሏቸውም ጠቁመዋል።

ከአገሪቱ ህዝብ 20 በመቶው ድርሻ ያለው አካል ጉዳተኛ በሌሎች መወከል ብቻ ሳይሆን በራሱ ውሳኔ ሰጭነት ተሳትፎው ሊረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከምክክር ኮሚሽኑ በሚሰራቸው ሥራዎች ሁሉ እንደ ዜጋና እንደ አካል ጉዳተኛ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ዕውቀትና ልምዱም እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከኮሚሽኑም ጋር በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ፍቃደኝነት አረጋግጠዋል።

ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት አካል ጉዳተኛውን ተደራሽ የማያደርጉ ናቸው ሲል ለአብነትም የምልክት ቋንቋን ያለመጠቀም ክፍተቶች እንደሆኑ አንስተዋል።

አባይነህ ጉጆ  ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ና ምህረት ንጉሴ ከፍቅር ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሌሎች ማህበራት ሀላፊዎች የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በተመለከተ ለኮሚሽኑ ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ከተዋቀረባቸው እሴቶች አንዱ ጉለልተኝነት፣ አካታችነትና አሳታፊነት መሆኑን ገልጸው አሰራሩም ከታች ወደ ላይ ነው ብለዋል።

"የአዕምሮ ጤና ችግር ታጋላጮችን ጨምሮ በእያንዳንዱ ቤተሰባችን ውስጥ አካል ጉዳተኞች አለን" ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የአካልና የአዕምሮ ጤና ጉዳተኞች አጀንዳ የሁሉም ጉዳይ ነው ብለዋል።

ዋናው የምክክሩ ዓላማ በማያግባቡና በሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲቻል ከታችኛው  ኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ አጀንዳዎችን ላይ የመፍትሄ ሃሳብ ማመቻቸት እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም ሂደት አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ የሚሆኑበትን አሰራር ገቢራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል እንደ አገር በጋራ ለመቀጠል በምክክር አጀንዳዎች አካታችነትና አሳታፊነት እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ የአካል ጉዳተኞች አጀንዳዎችም በምክክሩ መግባባት ተደርሶባቸው እንዲፈቱ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ-ሥላሴ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም የኅበረተሰብ ከፍል የራሳቸውን ድምጽ የሚያሰሙበት መድረክ እንደሚመቻች አረጋግጠዋል።

የምክክር ኮሚሽኑም ከአካል ጉዳተኞች አደረጃጀቶች ጋር በትብብር በመሥራት አገርን የማዳን ተልዕኮውን ለማሳካት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም