በማዕከላዊ ጎንደር 80 ሺህ ሄክታር የቅባት እህል ለማልማት እየተሰራ ነው

100

ጎንደር፤ ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ)፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ2014/15 የምርት ዘመን ለሀገር ኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የቅባት እህል በ80 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ግዛት ጀመረ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ገበያ ግብዓት የሚሆን የቅባት እህል ለማምረት እየተሰራ ነው።

በምርት ዘመኑ  አኩሪ አተር በ40 ሺህ ሄክታር ፣ ሰሊጥ በ30 ሺህ ሄክታርና ኑግ ደግሞ በ10 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ እንደሚለማ ተናግረዋል።

በልማቱም 30 ሺህ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ አመልክተው፤ ከእነዚህ ውስጥ 800 ያህሉ ባለሀብቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የቅባት እህል ልማቱ እንደ ሀገር የተከሰተውን የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

ልማቱ የግብርና ምርቶችን የኤክስፖርት እድገት ለማሳለጥ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችና አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግብዓት መቅረቡን አስታውቀዋል።

ለባለሀብቶችና ለአርሶ አደሮቹ አዳዲስ የግብርና  ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን የሚተገብሩበት ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ባለሀብቶቹና አርሶ አደሮቹ የእርሻ ማሳ ምንጣሮን ጨምሮ የመጀመሪያ ደረጃ ማሳ እያለሰለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በቅባት እህል ከሚሸፈነው መሬት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ሃላፊው አስታውቀዋል።

በምርት ዘመኑ ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በአኩሪ አተርና በሰሊጥ ለመሸፈን ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው” ያሉት ደግሞ የጠገዴ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት አስተባባሪ አቶ ድረስ ፈንታ ናቸው፡፡

 በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በጠገዴ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማራው ሀብቴ ጥላሁን የእርሻ ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቸሬ ገብሬ በበኩላቸው በምርት ዘመኑ በ521 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ አኩሪ አተር ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ ለ28 ቋሚና እስከ 3 ሺህ ለሚደርሱ የጉልበት ሠራተኞች ሥራ መፍጠሩን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ልማቱን ለማካሄድ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማህበሩ በልማቱ የሚያገኘውን ከ16 ሺህ ኩንታል በላይ አኩሪ አተር ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ማቀዱን አብራርተዋል፡፡

በዞኑ በ2014/15 ምርት ዘመን ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡