በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደን ላይ የሚደርሰው ህገ ወጥ ጭፍጨፋ እየቀነሰ መጥቷል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደን ላይ የሚደርሰው ህገ ወጥ ጭፍጨፋ እየቀነሰ መጥቷል ተባለ

ፍቼ ግንቦት 12/2ዐ14(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ህብረተሰቡን ያሳተፈ የደን ልማትና ጥበቃ ሥራ በመካሄዱ በደን ላይ የሚደርሰው ህገ ወጥ ጭፍጨፋና ውድመት መቀነሱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀቱም ተመልክቷል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ሂርጳሳ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ለእርሻ፣ ለማገዶ፣ ለቤት መስሪያና ማር ቆረጣ ሲባል በተፈጥሮ የደን ሀብት ላይ ይደርስ የነበረው ጭፍጨፋና ውድመት ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በእጅጉ ቀንሷል፡፡
ህብረተሰቡን ያሳተፈ የደን ልማትና ጥበቃ ሥራ መካሄዱና የህዝቡ የአካባቢ ተቆርቋሪነት እያደገ መምጣቱ ደግሞ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡
በዞኑ በተለይም ደራ፣ ሂደቡ አቦቴ፣ ወረ ጃርሶና ግራር ጃርሶ ወረዳዎች የደን ውጤቶችን ለመጠቀም ሲባል በየዓመቱ ከአስር ሄክታር በላይ የደን ሀብት በህገ ወጥ መንገድ ይጨፈጨፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በደን ጭፍጨፋና ውድመት የተመዘገበ ክስና ሪፖርት አለመኖሩን ለአብነት የጠቆሙት ምክትል ሃላፊው፤ በዚህም በዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ኘሮጀክት ውስጥ የታቀፉ 36 ሺህ ቤተሰቦች በጥበቃ ስራው አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ባለፈው ዓመት ከተተከሉ 231 ሚሊዮን ችግኞች መካከል ህብረተሰቡ ባደረገው እንክብካቤና ክትትል 79 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውን ነው የገለጹት፡፡
በዘንድሮ አመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ደግሞ ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ ሀገር በቀልና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው የዛፍ ችግኞች ተፈልተው ለተከላ መዘጋጀታቸውንም አቶ ሂርጳሳ ገልፀዋል፡፡

በዞኑ በመጪው ክረምት 54 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ የሚተከል ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ17ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ ሌሎች ለተከላ የሚረዱ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ምክትል ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በዚህም የአበሻ ጥድ፣ ዋንዛ፣ ግራርና ወይራን ጨምሮ ሌሎች ሀገር በቀል ዝርያ ያላቸው ችግኞች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት መኖ ዘር ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱንም አመልክተዋል፡፡
ችግኝ ለመትከል ከተዘጋጁት የግራር ጃርሶ ወረዳ ቶርባን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ሃይሉ ቦክስዮ ላለፉት አራት አመታት በማሳቸው አካባቢ ከተከሉት ችግኞች ከሽያጭ ብቻ የ4ዐ ሺህ ብር ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዘንድሮ አመትም ለእንስሳት መኖና ለሰው ምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት ለመትከል አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረጉ ጠቁመዋል፡፡
ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር በሽር ቃሲም በቡድንና በጋራ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን ጠቁመው በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር አካባቢያቸውን በደን ለማልበስ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡