በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የሚገኙ የማዕድን ሃብቶችን አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው

192

ጂንካ፤ግንቦት 12/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የሚገኙ የማዕድን ሃብቶችን አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለሀብቶችን ለመሳብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። 

የደቡብ ክልልና የዞኑ አመራሮች፣ ባለሀብቶችና ባለሙያዎች በዞኑ ሐመር ወረዳ የማዕድን ሃብት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ጎብኝተዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ የማዕድን ሀብቶቹን በመለየት በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ለመሳብ መሆኑ ተጠቁሟል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ቀርማ እንዳሉት በሀመር ወረዳ ኒስ፣ ኳርታይዝ፣ ማርብል፣ ፊልድ ስፓርና ዶሎማይት የተባሉ ማዕድናት በጆኦሎጂስቶች ጥናት እየተደረገባቸው ይገኛል።

በሐመር ወረዳ ካራ ዱስ፣ ሚኖ ገልቲ ቀበሌና በቱርሚ ዙሪያ ''ጎረምሳ ተራራ'' ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የሚገኘውን የእምነበረድ ማዕድን ክምችት ያለባቸው ቦታዎች የጉብኝቱ አካል ናቸው።

የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አፀደ አይዛ በበኩላቸው ማዕድናቱን በማልማት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲውሉ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በማዕድናቱ ዙሪያ የሚደረገው ጥናት በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ባለሀብቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ኤጀንሲው ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም